Psalms 38
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
አቤቱ፥ በቍጣህ አትቅሠፈኝ፥ በመዓትህም አትገሥጸኝ።
- 2
ፍላጾችህ ወግተውኛልና፥ እጅህንም አክብደህብኛልና።
- 3
ከቍጣህ የተነሣ ለሥጋዬ ጤና የለውም፤ ከኃጢአቴም የተነሣ ለአጥንቶቼ ሰላም የላቸውም።
- 4
ኃጢአቴ በራሴ ላይ ከፍ ከፍ ብሎአልና፥ እንደ ከባድ ሸክምም በላዬ ከብዶአልና።
- 5
ከስንፍናዬ የተነሣ ቍስሌ ሸተተ በሰበሰም፤
- 6
እጅግ ጐሰቈልሁ ተዋረድሁም፥ ሁልጊዜም በትካዜ እመላለሳለሁ።
- 7
ነፍሴ ስድብን ተሞልታለችና፥ ለሥጋዬም ጤና የላትምና።
- 8
ታመምሁ፤ እጅግም ተቸገርሁ፥ ከልቤ ውዝዋዜም የተነሣ ጮኽሁ።
- 9
አቤቱ፥ ፈቃዴ ሁሉ በፊትህ ነው፥ ጭንቀቴም ከአንተ አይሰወርም።
- 10
ልቤ ደነገጠብኝ፥ ኃይሌም ተወችኝ፥ የዓይኖቼም ብርሃን ፈዘዘ።
- 11
ወዳጆቼም ባልንጀሮቼም ከቍስሌ ገለል ብለው ቆሙ፥ ዘመዶቼም ርቀው ቆሙ።
- 12
ነፍሴንም የሚሹአት በረቱብኝ፥ መከራዬንም የሚፈልጉ ከንቱን ተናገሩ፥ ሁልጊዜም በሽንገላ ይመክራሉ።
- 13
እኔ ግን እንደማይሰማ ደንቆሮ አፉንም እንደማይከፍት ዲዳ ሆንሁ።
- 14
እንደማይሰማ ሰው በአፉም ተግሣጽ እንደሌለው ሰው ሆንሁ።
- 15
አቤቱ፥ በአንተ ታምኛለሁና፤ አቤቱ አምላኬ፥ አንተ ትሰማኛለህ።
- 16
ጠላቶቼ በእኔ ላይ ደስ እንዳይላቸው ብያለሁና፥ እግሮቼም ቢሰናከሉ ራሳቸውን በእኔ ላይ ከፍ ከፍ ያደርጋሉ።
- 17
እኔስ ወደ ማንከስ ቀርቤአለሁና፥ ቍስሌም ሁልጊዜም በፊቴ ነውና።
- 18
በደሌን እናገራለሁና፥ ስለ ኃጢአቴም እተክዛለሁ።
- 19
ጠላቶቼ ሕያዋን ናቸው ይበረቱብኝማል፥ በጠማማነትም የሚጠሉኝ በዙ።
- 20
ጽድቅን ስለ ተከተልሁ፥ በበጎ ፋንታ ክፉን የሚመልሱልኝ ይጠሉኛል።
- 21
አቤቱ፥ አንተ አትጣለኝ፤ አምላኬ፥ ከኔ አትራቅ።
- 22
አቤቱ መድኃኒቴ፥ እኔን ለመርዳት ፍጠን።