Psalms 37
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
በክፉዎች ላይ አትቅና፥ ዓመፃንም በሚያደርጉ ላይ አትቅና፤
- 2
እንደ ሣር ፈጥነው ይደርቃሉና፥ እንደ ለመለመ ቅጠልም ይረግፋሉና።
- 3
በእግዚአብሔር ታመን፥ መልካምንም አድርግ፥ በምድርም ተቀመጥ፥ ታምነህም ተሰማራ።
- 4
በእግዚአብሔር ደስ ይበልህ፥ የልብህንም መሻት ይሰጥሃል።
- 5
መንገድህን ለእግዚአብሔር አደራ ስጥ፥ በእርሱም ታመን፥ እርሱም ያደርግልሃል።
- 6
ጽድቅህን እንደ ብርሃን። ፍርድህንም እንደ ቀትር ያመጣል።
- 7
ለእግዚአብሔር ተገዛ ተስፋም አድርገው። መንገድም በቀናችለትና ጥመትን በሚያደርግ ሰው አትቅና።
- 8
ከቁጣ ራቅ መዓትንም ተው፤ እንዳትበድል አትቅና።
- 9
ክፉ አድራጊዎች ይጠፋሉና፤ እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን እነርሱ ምድርን ይወርሳሉ።
- 10
ገና ጥቂት፥ ኃጢአተኛም አይኖርም፤ ትፈልገዋለህ ቦታውንም አታገኝም።
- 11
ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፥ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል።
- 12
ኃጢአተኛ ጻድቁን ይመለካከተዋል፥ ጥርሱንም በእርሱ ላይ ያንገጫግጫል።
- 13
እግዚአብሔር ይሥቅበታል፥ ቀኑ እንደሚደርስ አይቶአልና።
- 14
ኃጢአተኞች ሰይፋቸውን መዘዙ፥ ቀስታቸውንም ገተሩ ድሀውንና ችግረኛውን ይጥሉ ዘንድ ልበ ቅኖችንም ይወጉ ዘንድ፤
- 15
ሰይፋቸው ወደ ልባቸው ይግባ፥ ቀስታቸውም ይሰበር።
- 16
ለጻድቅ ያለው ጥቂት ከብዙ ከኃጢአተኞች ሀብት ይበልጣል።
- 17
የኃጥአን ክንድ ትሰበራለችና፤ እግዚአብሔር ግን ጻድቃንን ይደግፋቸዋል።
- 18
የንጹሓንን መንገድ እግዚአብሔር ያውቃል፥ ርስታቸውም ለዘላለም ነው፤
- 19
በክፉ ዘመንም አያፍሩም በራብ ዘመንም ይጠግባሉ።
- 20
ኅጥአን ግን ይጠፋሉ፥ የእግዚአብሔር ጠላቶች በከበሩና ከፍ ከፍ ባሉ ጊዜ እንደ ጢስ ይጠፋሉ።
- 21
ኃጢአተኛ ይበደራል አይከፍልምም፤ ጻድቅ ግን ይራራል ይሰጣልም።
- 22
እርሱን የሚባርኩት ምድርን ይወርሳሉና፤ የሚረግሙት ግን ይጠፋሉ።
- 23
የሰው አካሄድ ከእግዚአብሔር ዘንድ ይጸናል፥ መንገዱንም ይወድዳል።
- 24
ቢወድቅም ለድንጋፄ አይጣልም፥ እግዚአብሔር እጁን ይዞ ይደግፈዋልና።
- 25
ጐለመስሁ አረጀሁም፤ ጻድቅ ሲጣል፥ ዘሩም እህል ሲለምን አላየሁም።
- 26
ሁልጊዜ ይራራል ያበድርማል፥ ዘሩም በበረከት ይኖራል።
- 27
ከክፉ ሽሽ፥ መልካምንም አድርግ፤ ለዘላለምም ትኖራለህ።
- 28
እግዚአብሔር ፍርዱን ይወድዳልና፥ ቅዱሳኑንም አይጥላቸውምና፤ ለዘላለምም ይጠብቃቸዋል ለንጹሓንም ይበቀልላቸዋል፤ የኅጥኣን ዘር ግን ይጠፋል።
- 29
ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፥ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ።
- 30
የጻድቅ አፍ ጥበብን ያስተምራል፥ አንደበቱም ፍርድን ይናገራል።
- 31
የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው፥ በእርምጃውም አይሰናከልም።
- 32
ኃጢአተኛ ጻድቁን ይመለከተዋል፥ ሊገድለውም ይወድዳል።
- 33
እግዚአብሔር ግን በእጁ አይተወውም፥ በተፋረደውም ጊዜ አያሸንፈውም።
- 34
እግዚአብሔርን ደጅ ጥና፥ መንገዱንም ጠብቅ፥ ምድርንም ትወርስ ዘንድ ከፍ ከፍ ያደርግሃል፤ ኃጢአተኞችም ሲጠፉ ታያለህ።
- 35
ኃጥአን ከፍ ከፍ ብሎ እንደ ሊባኖስ ዝግባም ለምልሞ አየሁት።
- 36
ብመለስ ግን አጣሁት፤ ፈለግሁት ቦታውንም አላገኘሁም።
- 37
ቅንነትን ጠብቅ፥ ጽድቅንም እይ፤ ለሰላም ሰው ቅሬታ አለውና።
- 38
በደለኞች በአንድነት ይጠፋሉ። የኃጢአተኞች ቅሬታ ይጠፋል።
- 39
የጻድቃን መድኃኒታቸው ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው፤ በመከራቸውም ጊዜ መጠጊያቸው እርሱ ነው።
- 40
እግዚአብሔር ይረዳቸዋል፥ ያድናቸዋልም፥ ከኃጢአተኞችም እጅ ያወጣቸዋል፥ ያድናቸዋል፥ በእርሱ ታምነዋልና።