Psalms 39
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ አልሁ።
- 2
ከዝምታ የተነሣ እንደ ዲዳ ሆንሁ፥ ለበጎ እንኳ ዝም አልሁ፥ ቍስሌም ታደሰብኝ።
- 3
ልቤም በውስጤ ሞቀብኝ፤ ከማሰቤም የተነሣ እሳት ነደደ፥ በአንደበቴም ተናገርሁ።
- 4
አቤቱ፥ ፍጻሜዬን አስታውቀኝ፥ የዘመኔ ቍጥሮች ምን ያህል እንደ ሆኑ፥ እኔ ምን ያህል ወደ ኋላ እንደምቀር አውቅ ዘንድ።
- 5
እነሆ፥ ዘመኖቼን አስረጀሃቸው፤ አካሌም በፊትህ እንደ ኢምንት ነው። ሕያው የሆነ ሰው ሁሉ በእውነት ከንቱ ብቻ ነው።
- 6
በከንቱ ይታወካል እንጂ በእውነት ሰው እንደ ጣላ ይመላለሳል፤ ያከማቻል የሚሰበስብለትንም አያውቅም።
- 7
አሁንስ ተስፋዬ ማን ነው? እግዚአብሔር አይደለምን? ትዕግሥቴም ከአንተ ዘንድ ነው።
- 8
ከኃጢአቴ ሁሉ አድነኝ፥ ለሰነፎችም ስድብ አታድርገኝ።
- 9
አንተ ሠርተኸኛልና ዝም አልሁ አፌንም አልከፈትሁም።
- 10
መቅሠፍትህን ከእኔ አርቅ፥ ከእጅህ ብርታት የተነሣ አልቄአለሁና።
- 11
በተግሣጽህ ስለ ኃጢአቱ ሰውን ዘለፍኸው፥ ነፍሱም እንደ ሸረሪት ድር ታልቃለች፤ በእውነት ሰው ሁሉ ከንቱ ነው።
- 12
አቤቱ፥ ጸሎቴን ስማ፥ ጩኸቴንም አድምጥ፥ ልቅሶዬንም ቸል አትበለኝ፤ እኔ በምድር ላይ መጻተኛ ነኝና፥ እንደ አባቶችም እንግዳ ነኝና።
- 13
ወደማልመለስበት ሳልሄድ ዐርፍ ዘንድ ተወኝ።