Genesis 30
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
ራሔልም ለያዕቆብ ልጆችን እንዳልወለደች ባየች ጊዜ በእኅትዋ ቀናችባት፤ ያቆብንም። ልጅ ስጠኝ፤ ይህስ ካልሆነ እሞታለሁ አለችው።
- 2
ያዕቆብም ራሔልን ተቆጥቶ። በውኑ እኔ የሆድን ፍሬ በነሣሽ በእግዚአብሔር ቦታ ነኝን? አላት።
- 3
እርስዋም ባሪያዬ ባላ እነሆ አለች፤ ድረስባት፤ በእኔም ጭን ላይ ትውለድ፥ የእርስዋም ልጆች ለእኔ ደግሞ ይሁኑልኝ አለች።
- 4
ባሪያዋን ባላንም ሚስት ትሆነው ዘንድ ለእርሱ ሰጠችው፤ ያዕቆብም ደረሰባት።
- 5
ባላም ፀነሰች፥ ወንድ ልጅንም ለያዕቆብ ወለደችለት።
- 6
ራሔልም። እግዚአብሔር ፈረደልኝ፥ ቃሌንም ደግሞ ሰማ፥ ወንድ ልጅንም ሰጠኝ አለች፤ ስለዚህ ስሙን ዳን ብላ ጠራችው።
- 7
የራሔልም ባሪያ ባላ ደግማ ፀነሰች፥ ለያዕቆብም ሁለተኛ ወንድ ልጅን ወለደች።
- 8
ራሔልም። ብርቱ ትግልን ከእኅቴ ጋር ታገልሁ፥ አሸነፍሁም አለች፤ ስሙንም ንፍታሌም ብላ ጠራችው።
- 9
ልያም መውለድን እንዳቆመች ባየች ጊዜ ባሪያዋን ዘለፋን ወሰደች፥ ሚስት ትሆነውም ዘንድ ለያዕቆብ ሰጠችው።
- 10
የልያ ባሪያ ዘለፋም ወንድ ልጅን ለያዕቆብ ወለደች።
- 11
ልያም። ጉድ አለች፤ ስሙንም ጋድ ብላ ጠራችው።
- 12
የልያ ባሪያ ዘለፋም ዳግመኛ ለያዕቆብ ወንድ ልጅን ወለደች።
- 13
ልያም። ደስታ ሆነልኝ፤ ሴቶች ያመሰግኑኛልና አለች፤ ስሙንም አሴር ብላ ጠራችው።
- 14
ሮቤል ስንዴ በሚታጨድበት ወራት ወጣ፥ በእርሻም እንኮይ አገኘ፥ ለእናቱ ለልያም አመጣላት። ራሔልም ልያን። የልጅሽን እንኮይ ስጪኝ አለቻት።
- 15
እርስዋም። ባሌን መውሰድሽ በውኑ ጥቂት ነገር ነውን? አሁን ደግሞ የልጄን እንኮይ ልትወስጂ ትፈልጊያለሽን? አለቻት። ራሔልም። እንኪያስ ስለ ልጅሽ እንኮይ በዚህች ሌሊት ከአንቺ ጋር ይተኛ አለች።
- 16
ያዕቆብም ሲመሽ ከዱር ገባ፥ ልያም ልትቀበለው ወጣች እንዲህም አለችው። ወደ እኔ ትገባለህ፤ በልጄ እንኮይ በእርግጥ ተከራይቼሃለሁና። በዚያችም ሌሊት ከእርስዋ ጋር ተኛ።
- 17
እግዚአብሔርም የልያን ጸሎት ሰማ፥ ፀነሰችም፥ አምስተኛ ወንድ ልጅንም ለያዕቆብ ወለደች።
- 18
ልያም። ባሪያዬን ለባሌ ስለ ሰጠሁ እግዚአብሔር ዋጋዬን ሰጠኝ አለች፤ ስሙንም ይሳኮር ብላ ጠራችው።
- 19
ልያም ደግማ ፀነሰች፥ ስድስተኛ ወንድ ልጅንም ለያዕቆብ ወለደች።
- 20
ልያም። እግዚአብሔር መልካም ስጦታን ሰጠኝ፤ እንግዲህስ ባሌ ከእኔ ጋር ይኖራል፥ ስድስት ልጆችን ወልጄለታለሁና አለች፤ ስሙንም ዛብሎን ብላ ጠራችው።
- 21
ከዚያም በኋላ ሴት ልጅን ወለደች፥ ስምዋንም ዲና አለቻት።
- 22
እግዚአብሔርም ራሔልን አሰበ፥ እግዚአብሔርም ተለመናት፥ ማኅፀንዋንም ከፈተላት፤
- 23
ፀነሰችም፥ ወንድ ልጅንም ወለደችና። እግዚአብሔር ስድቤን አስወገደ አለች፤
- 24
ስሙንም። እግዚአብሔር ሁለተኛ ወንድ ልጅን ይጨምርልኝ ስትል ዮሴፍ ብላ ጠራችው።
- 25
ራሔልም ዮሴፍን ከወለደች በኋላ ያዕቆብ ላባን እንዲህ አለው። ወደ ስፍራዬ ወደ አገሬም እመለስ ዘንድ አሰናብተኝ።
- 26
ስለ እነርሱ የተገዛሁላቸውን ሚስቶቼንና ልጆቼን ስጠኝና ልሂድ፤ የተገዛሁልህን መገዛት ታውቃለህና።
- 27
ላባም። በዓይንህ ፊት ሞገስን የማገኝ ብሆንስ ከዚሁ ተቀመጥ፤ እግዚአብሔር በአንተ ምክንያት እንደ ባረከኝ ተመልክቼአለሁና አለው።
- 28
ደመወዝህን ንገረኝ፥ እርሱንም እሰጥሃለሁ አለ።
- 29
እርሱም አለው። እንዴት እንዳገለገልሁህ፥ ከብትህንም እንዴት እንደ ጠበቅሁልህ አንተ ታውቃለህ።
- 30
ከእኔ መምጣት በፊት የነበረህ ጥቂት ነበርና፥ ዛሬም እጅግ በዛ፤ ወደ አንተ በመምጣቴም እግዚአብሔር ባረክህ፤ አሁንም እኔ ደግሞ ለቤቴ የምሠራው መቼ ነው?
- 31
እርሱም። የምሰጥህ ምንድር ነው? አለ። ያዕቆብም አለው። ምንም አትስጠኝ፤ ይህንም ነገር ብታደርግልኝ እንደ ገና በጎችህን አበላለሁ እጠብቃለሁም።
- 32
ዛሬ በመንጎችህ በኩል አልፋለሁ፥ በዚያም ከበጎችህ መካከል ዝንጕርጕርና ነቍጣ ያለበቱን ጥቁሩንም በግ ሁሉ፥ ከፍየሎቹም ነቍጣና ዝንጕርጕር ያለበቱን እለያለሁ፤ እነርሱም ደመወዜ ይሆናሉ።
- 33
ስለዚህም በፊትህ ያለውን ደመወዜን ለመመልከት በመጣህ ጊዜ ወደ ፊት ጻድቅነቴ ይመሰክርልኛል፤ ከፍየሎች ዝንጕርጕርና ነቍጣ የሌለበት ከበግ ጠቦቶችም ጥቁር ያልሆኑ ሁሉ፥ እርሱ በእኔ ዘንድ ቢገኝ እንደ ተሰረቀ ይቆጠርብኝ።
- 34
ላባም። እነሆ እንደ ቃልህ ይሁን አለ።
- 35
በዚያም ቀን ከተባቶቹ ፍየሎች ሽመልመሌ መሳይና ነቍጣ ያለባቸውን፥ ከእንስቶቹም ፍየሎች ዝንጕርጕርና ነቍጣ ያለባቸውን፥ ነጭ ያለበትን ማንኛውንም ሁሉ፥ ከበጎቹም መካከል ጥቁሩን በግ ሁሉ ለይቶ ለልጆቹ ሰጣቸው።
- 36
በእርሱና በያዕቆብ መካከልም የሦስት ቀን መንገድ ያህል አራቃቸው፤ ያዕቆብም የቀሩትን የላባን በጎች ይጠብቅ ነበር።
- 37
ያዕቆብም ልብን ለውዝ ኤርሞን ከሚባሉ እንጨቶች እርጥብ በትርን ወስዶ በበትሮቹ ውስጥ ያለው ነጭ እንዲታይ ነጭ ሽመልመሌ አድርጎ ላጣቸው።
- 38
የላጣቸውንም በትሮች በጎቹ ውኃ ሊጠጡ በመጡ ጊዜ በውኃ ማጠጫው ገንዳ ውስጥ በበጎቹ ፊት አኖራቸው፤ በጎቹ ውኃ ሊጠጡ በመጡ ጊዜ ይጎመጁ ነበር።
- 39
በጎቹም በትሮቹን አይተው ከመጎምጀታቸው የተነሣ ፀነሱ፤ በጎቹም ሽመልመሌ መሳይና ዝንጕርጕር ነቍጣም ያለበቱን ወለዱ።
- 40
ያዕቆብም ጠቦቶቹን ለየ፥ ሽመልመሌ መሳይና ጥቁር ያለባቸውን በጎቹንም ሁሉ በላባ በጎች ፊት ለፊት አኖረ፤ መንጎቹንም ለብቻቸው አቆማቸው፥ ወደ ላባም በጎች አልጨመራቸውም።
- 41
እንዲህም ሆነ፤ የበረቱት በጎች በጎመጁ ጊዜ፥ በጎቹ በትሮቹን አይተው በበትሮቹ አምሳል ይፀንሱ ዘንድ ያዕቆብ በትሮቹን በውኃ ማጠጫው ገንዳ ውስጥ ከበጎቹ ፊት አደረገ፤
- 42
በደከሙ በጎችም ፊት በትሩን አያደርገውም ነበር፤ የደከሙትም ለላባ፥ የበረቱትም ለያዕቆብ ሆኑ።
- 43
ያ ሰውም እጅግ ባለ ጠጋ ሆነ፤ ብዙም ከብት ሴቶችም ወንዶችም ባሪያዎች ግመሎችም አህዮችም ሆኑለት።