Genesis 29
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
ያዕቆብም ተነሥቶ ወደ ምሥራቅ ሰዎች አገር ሄደ።
- 2
በሜዳውም እነሆ ጕድጓድን አየ፥ በዚያም ሦስት የበጎች መንጎች በላዩ ተመስገው ነበር፤ ከዚያ ጕድጓድ በጎቹን ያጠጡ ነበርና፤ በጕድጓዱም አፍ የነበረው ድንጋይ ትልቅ ነበረ።
- 3
መንጎችም ሁሉ ከዚያ በተከማቹ ጊዜ ድንጋዩን ከጕድጓዱ አፍ ገለል አድርገው በጎቹን ያጠጡ ነበር፤ ድንጋዩንም ወደ ስፍራው መልሰው በጕድጓዱ አፍ እንደ ገና ይገጥሙት ነበር።
- 4
ያዕቆብም። ወንድሞቼ ሆይ፥ እናንት የወዴት ናችሁ? አላቸው። እነርሱም። እኛ የካራን ነን አሉት።
- 5
የናኮርን ልጅ ላባን ታውቁታላችሁን? አላቸው። እነርሱም። እናውቀዋለን አሉት።
- 6
እርሱ። ደኅና ነውን? አላቸው። እነርሱም። አዎን ደኅና ነው፤ አሁንም ልጁ ራሔል ከበጎች ጋር መጣች አሉት።
- 7
እርሱም። ቀኑ ገና ቀትር ነው፥ ከብቶቹ የሚከማቹበት ሰዓቱም ገና አልደረሰም፤ አሁንም በጎቹን አጠጡና ሄዳችሁ አሰማሩአቸው አላቸው።
- 8
እነርሱም አሉ። መንጎች ሁሉ እስኪከማቹና ድንጋዩን ከጕድጓዱ አፍ እስኪገለብጡት ድረስ አንችልም፤ ከዚያም በኋላ በጎቹን እናጠጣለን።
- 9
እርሱም ገና ከእነርሱ ጋር ሲነጋገር እነሆ የላባ ልጅ ራሔል ከአባትዋ በጎች ጋር ደረሰች፤ እርስዋ የአባትዋን በጎች ትጠብቅ ነበርና።
- 10
ያዕቆብም የእናቱን ወንድም የላባን ልጅ ራሔልንና የእጎቱን የላባን በጎች ባየ ጊዜ፥ ቀረበ ከጕድጓዱም አፍ ድንጋዩን ገለበጠ፥ የአጎቱን የላባን በጎችንም አጠጣ።
- 11
ያዕቆብም ራሔልን ሳማት፥ ቃሉንም ከፍ አድርጎ አለቀሰ።
- 12
ያዕቆብም የአባትዋ ዘመድና የርብቃ ልጅ መሆኑን ለራሔል አስታወቃት፤ እርስዋም ሮጣ ሄዳ ለአባትዋ ይህን ነገር ነገረችው።
- 13
ላባም የእኅቱን ልጅ የያዕቆብን ወሬ በሰማ ጊዜ ሊቀበለው ሮጠ፥ አቅፎም ሳመው፥ ወደ ቤቱም አገባው። ነገሩንም ሁሉ ለላባ ነገረው ።
- 14
ላባም። በእውነት አንተ አጥንቴ ሥጋዬም ነህ አለው። አንድ ወር የሚያህልም ከእርሱ ጋር ተቀመጠ።
- 15
ላባም ያዕቆብን። ወንድሜ ስለሆንህ በከንቱ ታገለግለኛለህን? ምንዳህ ምንድር ነው? ንገረኝ አለው።
- 16
ለላባም ሁለት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ የታላቂቱ ስም ልያ የታናሺቱ ስም ራሔል ነበረ።
- 17
ልያም ዓይነ ልም ነበረች፤ ራሔል ግን መልከ መልካም ነበረች ፊትዋም ውብ ነበረ።
- 18
ያዕቆብም ራሔልን ወደደ፤ እንዲህም አለ። ስለ ታናሺቱ ልጅህ ስለ ራሔል ሰባት ዓመት እገዛልሃለሁ።
- 19
ላባም። ለሌላ ሰው ከምሰጣት ይልቅ ለአንተ ብሰጣት ይሻላል፤ ከእኔ ጋር ተቀመጥ አለ።
- 20
ያዕቆብም ስለ ራሔል ሰባት ዓመት ተገዛ፤ እርስዋንም ይወድዳት ስለነበረ በእርሱ ዘንድ እንደ ጥቂት ቀን ሆነለት።
- 21
ያዕቆብም ላባን። ወደ እርስዋ እገባ ዘንድ ሚስቴን ስጠኝ፥ ቀኔ ተፈጽሞአልና አለው።
- 22
ላባም የዚያን ስፍራ ሰዎች ሁሉ ሰበሰበ፥ ሰርግም አደረገ።
- 23
በመሸም ጊዜ ልጁን ልያን ወስዶ ለያዕቆብ አገባለት፤ ያዕቆብም ወደ እርስዋ ገባ።
- 24
ላባም ለልጁ ለልያ ባሪያይቱን ዘለፋን ባርያ ትሆናት ዘንድ ሰጣት።
- 25
በነጋም ጊዜ እነሆ ልያ ሆና ተገኘች፤ ላባንም። ምነው እንደዚህ አደረግህብኝ? ያገለገልሁህ ስለ ራሔል አልነበረምን? ለምን አታለልኸኝ? አለው።
- 26
ላባም እንዲህ አለ። በአገራችን ታላቂቱ ሳለች፥ ታናሺቱን እንሰጥ ዘንድ ወግ አይደለም፤
- 27
ይህችንም ሳምንት ፈጽም፤ ሌላ ሰባት ዓመት ደግሞ እኔን ስለምታገለግለኝ አገልግሎት እርስዋን ደግሞ እሰጥሃለሁ።
- 28
ያዕቆብም እንዲህ አደረገ፥ ይህችንም ሳምንት ፈጸመ፤ ልጁን ራሔልንም ለእርሱ ሚስት ትሆን ዘንድ ሰጠው።
- 29
ላባም ለልጁ ለራሔል ባርያይቱን ባላን ባርያ ትሆናት ዘንድ ሰጣት ።
- 30
ያዕቆብም ወደ ራሔል ደግሞ ገባ። ራሔልንም ከልያ ይልቅ ወደዳት፤ ሌላ ሰባት ዓመትም ተገዛለት።
- 31
እግዚአብሔርም ልያ የተጠላች መሆንዋን ባየ ጊዜ ማኅፀንዋን ከፈተላት፤ ራሔል ግን መካን ነበረች።
- 32
ልያም ፀነሰች፥ ወንድ ልጅንም ወለደች፥ ስሙንም ሮቤል ብላ ጠራችው፤ እግዚአብሔር መከራዬን አይቶአልና፥ እንግዲህም ወዲህ ባሌ ይወድደኛል ብላለችና።
- 33
ደግሞም ፀነሰች፥ ወንድ ልጅንም ወለደች፤ እኔ እንደ ተጠላሁ እግዚአብሔር ስለ ሰማ ይህን ደገመኝ አለች፤ ስሙንም ስምዖን ብላ ጠራችው።
- 34
ደግሞም ፀነሰች፥ ወንድ ልጅንም ወለደች፤ አሁንም ባሌ ወደ እኔ ይጠጋል፥ ሦስት ወንዶች ልጆችን ወልጄለታለሁና አለች፤ ስለዚህም ስሙን ሌዊ ብላ ጠራችው።
- 35
ደግሞም ፀነስች፥ ወንድ ልጅንም ወለደች፤ በዚህም ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ አለች፤ ስለዚህም ስሙን ይሁዳ ብላ ጠራችው። መውለድንም አቆመች።