Genesis 31
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
ያዕቆብም የላባ ልጆች ያሉትን ነገር። ያዕቆብ ለአባታችን የሆነውን ሁሉ ወሰደ፤ ይህንም ሁሉ ክብር ከአባታችን ከብት አገኘ ሲሉ ሰማ።
- 2
ያዕቆብም የላባን ፊት አየ፥ እነሆም ከእርሱ ጋር እንደ ዱሮው አልሆነም።
- 3
እግዚአብሔርም ያዕቆብን። ወደ አባትህ ምድር ወደ ዘመዶችህም ተመለስ፤ ከአንተም ጋር እሆናለሁ አለው።
- 4
ያዕቆብም ልኮ ራሔልንና ልያን ወደ በጎቹ ስፍራ ወደ ሜዳ ጠራቸው፥
- 5
እንዲህም አላቸው። የአባታችሁ ፊት ከእኔ ጋር እንደ ዱሮ እንዳልሆነ አያለሁ፤ ነገር ግን የአባቴ አምላክ ከእኔ ጋር ነው።
- 6
እኔ ባለኝ ጕልበቴ ሁሉ አባታችሁን እንዳገለገልሁ ታውቃላችሁ።
- 7
አባታችሁ ግን አታለለኝ፥ ደመወዜንም አሥር ጊዜ ለወጠ፤ እግዚአብሔር ግን ክፉ ያደርግብኝ ዘንድ አልፈቀደለትም።
- 8
ደመወዝህ ዝንጕርጕሮች ይሁኑ ቢለኝ በጎቹ ሁሉ ዝንጕርጕሮችን ወለዱ፤ ሽመልመሌ መሳዮቹ ደመወዝህ ይሁኑ ቢለኝ በጎቹ ሁሉ ሽመልመሌ መሳዮችን ወለዱ።
- 9
እግዚአብሔርም የአባታችሁን በጎች ሁሉ ነሥቶ ለእኔ ሰጠኝ።
- 10
እንዲህም ሆነ፤ በጎቹ በጎመጁ ጊዜ ዓይኔን አንሥቼ በሕልም አየሁ፤ እነሆም፥ በበጎችና በፍየሎች ላይ የሚንጠላጠሉት የበጎችና የፍየሎች አውራዎች ሽመልመሌ መሳዮችና ዝንጕርጕሮች ነቁጣ ያለባቸውም ነበሩ።
- 11
የእግዚአብሔርም መልአክ በሕልም። ያዕቆብ ሆይ አለኝ፤ እኔም። እነሆኝ አልሁት።
- 12
እንዲህም አለኝ። ዓይንህን አቅንተህ እይ፤ በበጎችና በፍየሎች ላይ የሚንጠላጠሉት የበጎችና የፍየሎች አውራዎች ሽመልመሌ መሳዮችና ዝንጕርጕሮች ነቁጣ ያለባቸውም ናቸው፤ ላባ በአንተ ላይ የሚያደርገውን ሁሉ አይቼአለሁና።
- 13
ሐውልት የቀባህበት በዚያም ለእኔ ስእለት የተሳልህበት የቤቴል አምላክ እኔ ነኝ፤ አሁንም ተነሥተህ ከዚህ አገር ውጣ፥ ወደ ተወለድህበትም ምድር ተመለስ።
- 14
ራሔልና ልያም መልሰው እንዲህ አሉት። በአባታችን ቤት ለእኛ ድርሻና ርስት በውኑ ቀርቶልናልን?
- 15
እኛ በእርሱ ዘንድ እንደ ባዕድ የተቈጠርን አይደለንምን? እርሱ እኛን ሸጦ ዋጋችንን በልቶአልና።
- 16
ስለዚህም እግዚአብሔር ከአባታችን የነሣው ይህ ሁሉ ሀብት ለእኛና ለልጆቻችን ነው፤ አሁንም እግዚአብሔር ያለህን ሁሉ አድርግ።
- 17
ያዕቆብም ተነሣ፥ ልጆቹንና ሚስቶቹንም በግመሎች ላይ አስቀመጠ፤
- 18
መንጎቹንም ሁሉ፥ የቤቱንም ዕቃ ሁሉ፥ በሁለት ወንዞች መካከል ሳለ ያገኛቸውን ከብቶች ሁሉ ይዞ ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅ ወደ ከነዓን ምድር ሄደ።
- 19
ላባ ግን በጎቹን ለመሸለት ሄዶ ነበር፤ ራሔልም የአባትዋን ተራፊም ሰረቀች።
- 20
ያዕቆብም የሶርያውን ሰው ላባን ከድቶ ኮበለለ፥ መኮብለሉንም፥ አልነገረውም።
- 21
እርሱም ያለውን ሁሉ ይዞ ኮበለለ፤ ተነሥቶም ወንዙን ተሻገረ፥ ፊቱንም ወደ ገለዓድ ተራራ አቀና።
- 22
በሦስተኛውም ቀን የያዕቆብ መኮብለል ለላባ ተነገረው።
- 23
ከወንድሞቹም ጋር ሆኖ የሰባት ቀን መንገድ ያህል ተከተለው፥ በገለዓድ ተራራም ላይ ደረሰበት።
- 24
እግዚአብሔርም ወደ ሶርያው ሰው ወደ ላባ በሌሊት ሕልም መጥቶ። ያዕቆብን በክፉ ነገር እንዳትናገረው ተጠንቀቅ አለው።
- 25
ላባም ደረሰበት፤ ያዕቆብም ድንኳኑን በተራራው ተክሎ ነበር፤ ላባም ከወንድሞቹ ጋር በገለዓድ ተራራ ድንኳኑን ተከለ።
- 26
ላባም ያዕቆብን አለው። ለምን እንዲህ አደረግህ? ከእኔ ከድተህ ኮበለልህ፥ ልጆቼንም በሰይፍ እንደ ተማረኩ ዓይነት ነዳሃቸው።
- 27
ስለምን በስውር ሸሸህ? ከእኔም ከድተህ ስለምን ኮበለልህ? በደስታና በዘፈን በከበሮና በበገና እንድሰድድህ ለምን አልነገርኸኝም?
- 28
ወንዶቹንና ሴቶቹን ልጆቼን እንድስም ስለ ምን አልፈቀድህልኝም? ይህንም በስንፍና አደረግህ።
- 29
ክፉ አደርግባችሁ ዘንድ ኃይል ነበረኝ፤ ነገር ግን የአባታችሁ አምላክ ትናንት። ያዕቆብን በክፉ ነገር እንዳትናገረው ተጠንቀቅ ብሎ ነገረኝ።
- 30
አሁንም የአባትህን ቤት ከናፈቅህ ሂድ፤ ነገር ግን አምላኮቼን ለምን ሰረቅህ?
- 31
ያዕቆብም መለሰ ላባንም እንዲህ አለው። ልጆችህን ከእኔ የምትቀማኝ ስለመሰለኝና ስለፈራሁ ይህን አደረግሁ።
- 32
አምላኮችህን የምታገኝበት ሰው ግን እርሱ ይሙት፤ የአንተ የሆነውም በእኔ ዘንድ ይገኝ እንደ ሆነ በወንድሞቻችን ፊት ፈልግ፥ ለአንተም ውሰደው አለ። ራሔል እንደ ሰረቀቻቸው ያዕቆብ አያውቅም ነበርና።
- 33
ላባም ወደ ያዕቆብ ድንኳንና ወደ ልያ ድንኳን ወደ ሁለቱም ባሪያዎች ድንኳን ገባ፥ ነገር ግንአላገኘም። ከልያም ድንኳን ወጥቶ ወደ ራሔል ድንኳን ገባ።
- 34
ራሔልም ተራፊምን ወስዳ ከግመል ኮርቻ በታች ሸሸገች፥ በላዩም ተቀመጠችበት። ላባም ድንኳኑን ሁሉ ፈለገ፥ አንዳችም አላገኘም።
- 35
እርስዋም አባትዋን። በፊትህ ለመቆም ስላልቻልሁ አትቆጣብኝ፤ በሴቶች የሚደርስ ግዳጅ ደርሶብኛልና አለችው። እርሱም ፈለገ፥ ነገር ግን ተራፊምን አላገኘም።
- 36
ያዕቆብም ተቆጣ ላባንም ወቀሰው፤ ያዕቆብም መለሰ ላባንም እንዲህ አለው። የበደልሁህ በደል ምንድር ነው ኃጢአቴስ ምንድር ነው ይህን ያህል ያሳደድኸኝ
- 37
አሁንም ዕቃዬን ሁሉ በረበርህ፤ ከቤትህስ ዕቃ ሁሉ ምን አገኘህ እነርሱ በእኛ በሁለታችን መካከል ይፈርዱ ዘንድ በወንድሞቼና በወንድሞችህ ፊት አቅርበው።
- 38
ሀያ ዓመት ሙሉ ከአንተ ጋር ነበርሁ፤ በጎችህና ፍየሎችህ አልጨነገፉም፤ የመንጎችህንም ጠቦቶች አልበላሁም፤ አውሬ የሰበረውን አላመጣሁልህም ነበር፤
- 39
እኔ ስለ እርሱ እከፍልህ ነበርሁ፤ በቀንም በሌሊትም የተሰረቀውን ከእጄ ትሻው ነበርህ።
- 40
የቀን ሐሩር የሌሊት ቍር ይበላኝ ነበር፥ እንቅልፍም ከዓይኔ ጠፋ። 4
- 41
እንዲሁ በአንተ ቤት ሀያ ዓመት ነበርሁ አሥራ አራት ዓመት ስለ ሁለቱ ሴቶች ልጆችህ፥ ስድስት ዓመትም ስለ በጎችህ ተገዛሁልህ፤ ደመወዜንም አሥር ጊዜ ለዋወጥኸው።
- 42
የአባቴ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም ፍርሃት ከእኔ ጋር ባይሆንስ ዛሬ ባዶ እጄን በሰደድኸኝ ነበር፤ እግዚአብሔር መከራዬንና የእጆቼን ድካም አየ፥ ትናንትም ገሠጸህ።
- 43
ላባም እንዲህ ብሎ ለያቆብ መለሰለት። ሴቶቹ ልጆች ልጆቼ ናቸው፥ ሕፃናቱም ሕፃናቴ ናቸው፥ መንጎቹም መንጎቼ ናቸው፥ የምታየውም ሁሉ የእኔ ነው፤ ዛሬም በእነዚህ በሴቶች ልጆቼና በወለዱአቸው ልጆቻቸው ላይ ምን ላደርግ ይቻላል
- 44
አሁንም ና፥ አንተና እኔ ቃል ኪዳን እንጋባ፤ በእኔና በአንተ መካከልም ምስክር ይሁን።
- 45
ያዕቆብም ድንጋይ ወስዶ ሐውልት አቆመ።
- 46
ያዕቆብም ወንድሞቹን። ድንጋይ ሰብስቡ አላቸው፤ እነርሱም ድንጋይ ሰብስበው ከመሩ፤ በድንጋዩም ክምር ላይ በሉ።
- 47
ላባም ይጋር ሠሀዱታ ብሎ ጠራት፤ ያዕቆብም ገለዓድ አላት።
- 48
ላባም። ይህች ክምር በእኔና በአንተ መካከል ዛሬ ምስክር ናት አለ። ስለዚህም ስምዋ ገለዓድ ተባለ፤
- 49
ደግሞም ምጽጳ ተባለ። እኛ በተለያየን ጊዜ እግዚአብሔር በእኔና በአንተ መካከል ሆኖ ይጠብቅ ብሎአልና።
- 50
ልጆቼን ብትበድላቸው ወይም በላያቸው ሚስቶችን ብታገባባቸው ከእኛ ጋር ያለ ሰው የለም፤ እግዚአብሔር በእኔና በአንተ መካከል ምስክር ነው።
- 51
ላባም ያዕቆብን አለው። በእኔና በአንተ መካከል እነሆ ይህች ክምር፥ እነሆም ያቆምኋት ሐውልት፤
- 52
እኔ ወደ አንተ ይህችን ክምር እንዳላልፍ፥ አንተም ለክፋት ወደ እኔ ይህችን ክምርና ይህችን ሐውልት እንዳታልፋት፥ ይህች ክምር ምስክር ናት፥ ይህችም ሐውልት ምስክር ናት።
- 53
የአብርሃም አምላክ የናኮርም አምላክ የአባታቸውም አምላክ በእኛ መካከል ይፍረድ። ያዕቆብም በአባቱ በይስሐቅ ፍርሃት ማለ።
- 54
ያዕቆብም በተራራው ላይ መሥዋዕትን ሠዋ፥ ወንድሞቹንም እንጀራ እንዲበሉ ጠራ፤ እነርሱም እንጀራን በሉ፥ በዚያም በተራራ አደሩ።
- 55
ላባም ማልዶ ተነሥቶ ወንዶቹንና ሴቶቹን ልጆቹን ሳመ ባረካቸውም፤ ላባም ተመልሶ ወደ ስፍራው ሄደ።