Exodus 6
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። በጸናች እጅ ይለቅቃችኋልና፥ በጸናችም እጅ ከምድሩ አስወጥቶ ይሰድዳቸዋልና አሁን በፈርዖን የማደርገውን ታያለህ።
- 2
እግዚአብሔርም ሙሴን ተናገረው አለውም። እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤
- 3
ለአብርሃምም ለይስሐቅም ለያዕቆብም ሁሉን እንደሚችል አምላክ ተገለጥሁ፤ ነገር ግን ስሜ እግዚአብሔር አልታወቀላቸውም ነበር።
- 4
የተሰደዱባትንም ምድር፥ የእንግድነታቸውን የከነዓንን ምድር፥ እሰጣቸው ዘንድ ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳኔን አቆምሁ።
- 5
ደግሞ እኔ ግብፃውያን የገዙአቸውን የእስራኤልን ልጆች ልቅሶ ሰማሁ፤ ቃል ኪዳኔንም አሰብሁ።
- 6
ስለዚህም ለእስራኤል ልጆች እንዲህ በላቸው። እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ ከግብፃውያንም ባርነት አወጣችኋለሁ፥ ከተገዥነታቸውም አድናችኋለሁ፤ በተዘረጋ ክንድ በታላቅ ፍርድም እታደጋችኋለሁ፥
- 7
ለእኔም ሕዝብ እንድትሆኑ እቀበላችኋለሁ፥ አምላክም እሆናችኋለሁ፤ እኔም ከግብፃውያን ባርነት ያወጣኋችሁ እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።
- 8
ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም እሰጣት ዘንድ ወደ ማልሁባት ምድር አገባችኋለሁ፤ እርስዋንም ርስት አድርጌ እሰጣችኋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
- 9
ሙሴም ይህን ለእስራኤል ልጆች ተናገረ፤ እነርሱ ግን ከሰውነታቸው መጨነቅ ከከባዱም ሥራ የተነሣ ቃሉን አልሰሙትም።
- 10
እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
- 11
ግባ፥ የእስራኤልንም ልጆች ከአገሩ ይለቅቅ ዘንድ ለግብፅ ንጉሥ ለፈርዖን ንገር።
- 12
ሙሴም በእግዚአብሔር ፊት። እነሆ የእስራኤል ልጆች አልሰሙኝም፤ እንዴትስ ፈርዖን ይሰማኛል? ይልቁንም እኔ ከንፈረ ቈላፍ ነኝ ብሎ ተናገረ።
- 13
እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን ተናገራቸው፥ የግብፅ ንጉሥ ፈርዖንም የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ እንዲያወጣቸው ይነግሩት ዘንድ አዘዛቸው።
- 14
የአባታቸውም ቤት አለቆች እነዚህ ናቸው። የእስራኤል የበኵር ልጅ የሮቤል ልጆች፤ ሄኖኅ፥ ፈሉስ፥ አስሮን፥ ከርሚ፤ እነዚህ የሮቤል ወገኖች ናቸው።
- 15
የስምዖንም ልጆች፤ ይሙኤል፥ ያሚን፥ ኦሃድ፥ ያኪን፥ ዶሐር፥ የከነዓናዊቱም ልጅ ሳኡል፤ እነዚህ የስምዖን ወገኖች ናቸው።
- 16
እነዚህም እንደ ወገኖቻቸው የሌዊ ልጆች ስሞች ጌድሶን፥ ቀዓት፥ ሜራሪ ናቸው። የሌዊም የሕይወት ዘመን መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ነው።
- 17
የጌድሶንም ልጆች እንደ ወገኖቻቸው ሎቤኒ፥ ሰሜኢ ናቸው።
- 18
የቀዓትም ልጆች እንበረም፥ ይስዓር፥ ኬብሮን፥ ዑዝኤል ናቸው፤ የቀዓትም የሕይወቱ ዘመን መቶ ሠላሳ ሦስት ዓመት ነው።
- 19
የሜራሪ ልጆች ሞሖሊ፥ ሙሲ ናቸው። እነዚህ እንደ ትውልዳቸው የሌዊ ወገኖች ናቸው።
- 20
እንበረምም የአጎቱን ልጅ ዮካብድን አገባ፥ አሮንና ሙሴንም ወለደችለት፤ የእንበረምም የሕይወቱ ዘመን መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ነው።
- 21
የይስዓር ልጆች ቆሬ፥ ናፌግ፥ ዝክሪ ናቸው።
- 22
የዑዝኤል ልጆች ሚሳኤል፥ ኤልዳፋን፥ ሥትሪ ናቸው።
- 23
አሮንም የአሚናዳብን የነአሶንን እኅት ኤልሳቤጥን አገባ፥ እርስዋም ናዳብንና አብዮድን አልዓዛርንና ኢታምርን ወለደችለት።
- 24
የቆሬ ልጆች አሴር፥ ሕልቃና፥ አብያሳፍ ናቸው፤ እነዚህ የቆሬ ልጆች ወገኖች ናቸው።
- 25
የአሮንም ልጅ አልዓዛር ከፉትኤል ልጆች ሚስት አገባ፥ እርስዋም ፊንሐስን ወለደችለት። እነዚህ እንደ ወገኖቻቸው የሌዋውያን አባቶች አለቆች ናቸው።
- 26
እነዚህ አሮንና ሙሴ እግዚአብሔር። ከግብፅ ምድር በየሠራዊቶቻቸው የእስራኤልን ልጆች አውጡ ያላቸው ናቸው።
- 27
እነዚህ የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ ያወጡ ዘንድ ከግብፅ ንጉሥ ከፈርዖን ጋር የተነጋገሩ ናቸው፤ እነዚህ ሙሴና አሮን ናቸው።
- 28
እግዚአብሔርም በግብፅ አገር ሙሴን በተናገረው ቀን እንዲህ ሆነ፤
- 29
እግዚአብሔር ሙሴን። እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ እኔ የምነግርህን ሁሉ ለግብፅ ንጉሥ ለፈርዖን ንገር ብሎ ተናገረው።
- 30
ሙሴም በእግዚአብሔር ፊት። እነሆ እኔ ከንፈረ ቈላፍ ነኝ፤ እንዴትስ ፈርዖን ይሰማኛል? አለ።