Exodus 5
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
ከዚህም በኋላ ሙሴና አሮን መጥተው ፈርዖንን እንዲህ አሉት። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በምድረ በዳ በዓል ያደርግልኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ።
- 2
ፈርዖንም። ቃሉን እሰማ ዘንድ እስራኤልንስ እለቅቅ ዘንድ እግዚአብሔር ማን ነው? እግዚአብሔርን አላውቅም፥ እስራኤልንም ደግሞ አልለቅቅም አለ።
- 3
እነርሱም። የዕብራውያን አምላክ ተገናኘን፤ ቸነፈር ወይም ሰይፍ እንዳይጥልብን የሦስት ቀን መንገድ በምድረ በዳ እንድንሄድ፥ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር እንድንሠዋ እንለምንሃለን አሉት።
- 4
የግብፅ ንጉሥም። አንተ ሙሴ አንተም አሮን፥ ሕዝቡን ለምን ሥራቸውን ታስተዋላችሁ? ወደ ተግባራችሁ ሂዱ አላቸው።
- 5
ፈርዖንም። እነሆ የምድሩ ሕዝብ አሁን በዝቶአል፥ እናንተም ሥራቸውን ታስፈቱአቸዋላችሁ አለ።
- 6
ፈርዖንም በዚያን ቀን የሕዝቡን አስገባሪዎች ሹማምቶቹንም እንዲህ ሲል አዘዘ።
- 7
እንደ ወትሮው ለጡብ ሥራ ደግሞ ገለባ ለሕዝቡ አትስጡ፤ ነገር ግን እነርሱ ሄደው ገለባ ይሰብስቡ።
- 8
ቀድሞ ያደርጉት የነበረውን የጡብ ቍጥር በእነርሱ ላይ አድርጉት፤ ምንም ከእርሱ አታጕድሉ፤ ሥራ ሰልችተዋልና ስለዚህ። ለአምላካችን እንድንሰዋ እንሂድ እያሉ ይጮኻሉ።
- 9
እርሱንም ያደርጉ ዘንድ በሰዎች ላይ ሥራው ይክበድባቸው፤ ከንቱ ቃልም አያስቡ።
- 10
የሕዝቡም አስገባሪዎች ሹማምቶቹም ወጡ፥ ሕዝቡንም። ፈርዖን እንዲህ ይላል። ገለባ አልሰጣችሁም።
- 11
እናንተ ሂዱ፥ ከምታገኙበትም ስፍራ ገለባ ሰብስቡ፤ ከሥራችሁ ግን ምንም አይጐድልም አሉአቸው።
- 12
ሕዝቡም ስለ ገለባ እብቅ ሊሰበስቡ በግብፅ ምድር ሁሉ ተበተኑ።
- 13
አስገባሪዎቹም። ገለባ ትቀበሉበት እንደ ነበረ ጊዜ የቀን ሥራችሁን ጨርሱ እያሉ አስቸኰሉአቸው።
- 14
የፈርዖንም አስገባሪዎች። ቀድሞ ታደርጉ እንደ ነበራችሁ ትናንትናና ዛሬ የተቈጠረውን ጡብ ስለ ምን አትጨርሱም? እያሉ በእስራኤል ልጆች ላይ የተሾሙትን አለቆቹን ገረፉ።
- 15
የእስራኤል ልጆች አለቆችም ወደ ፈርዖን መጡ። ለምን በባሪያዎችህ እንዲህ ታደርጋለህ?
- 16
ገለባ አይሰጡንም፥ የጡቡንም ሥራ እንድንሠራ ያዝዙናል፤ እነሆም ባሪያዎችህን ይገርፉናል፤ ግድፈቱ ግን በአንተ ሕዝብ ላይ ነው ብለው ጮኹ።
- 17
እርሱ ግን። ሰልችታችኋል፥ ሰልችታችኋል፤ ስለዚህም። እንሂድ ለእግዚአብሔርም እንሠዋ ትላላችሁ።
- 18
አሁንም ሂዱ፥ ሥሩ፤ ገለባ አይሰጡአችሁም፥ የጡቡን ቍጥር ግን ታመጣላችሁ አላቸው።
- 19
የእስራኤልም ልጆች አለቆች። ዕለት ዕለት ከምትሰሩት ከጡቡ ቍጥር ምንም አታጕድሉ ባሉአቸው ጊዜ ነገሩ እንደ ከፋባቸው አዩ።
- 20
ከፈርዖንም ዘንድ ሲወጡ ሙሴንና አሮንን በፊታቸው ቆመው ተገናኙአቸው።
- 21
እነርሱም። በፈርዖንና በባሪያዎቹ ፊት ሽታችንን አግምታችሁታልና፥ ይገድሉንም ዘንድ ሰይፍን በእጃቸው ሰጥታችኋቸዋልና እግዚአብሔር ይመልከታችሁ ይፍረድባችሁም አሉአቸው።
- 22
ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ተመለሰና። ጌታ ሆይ፥ ስለ ምን ይህን ሕዝብ አስከፋህ? ስለ ምንስ ላክኸኝ?
- 23
በስምህ እናገር ዘንድ ወደ ፈርዖን ከገባሁ ወዲህ፥ ይህን ሕዝብ አስከፍቶታልና፤ አንተም ሕዝብህን ከቶ አላዳንኸውም አለ።