Exodus 7
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። እይ፥ እኔ ለፈርዖን አምላክ አድርጌሃለሁ፤ ወንድምህም አሮን ነቢይ ይሆንልሃል።
- 2
ያዘዝሁህን ነገር ሁሉ አንተ ትነግረዋለህ፤ ወንድምህም አሮን የእስራኤልን ልጆች ከአገሩ ይለቅቅ ዘንድ ከፈርዖን ጋር ይናገራል።
- 3
እኔም የፈርዖንን ልብ አጸናለሁ፥ በግብፅ ምድርም ድንቄንና ተአምራቴን አበዛለሁ።
- 4
ፈርዖንም አይሰማችሁም፥ እጄንም በግብፅ ላይ አደርጋለሁ፥ ሠራዊቴንም የእስራኤልን ልጆች ሕዝቤን በታላቅ ፍርድ ከግብፅ አገር አወጣለሁ።
- 5
ግብፃውያንም፥ እጄን በግብፅ ላይ በዘረጋሁ ጊዜ፥ የእስራኤልንም ልጆች ከመካከላቸው ባወጣሁ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆነሁ ያውቃሉ።
- 6
ሙሴና አሮንም እንዲህ አደረጉ፤ እግዚአብሔር እንዳዘዛቸው አደረጉ።
- 7
ፈርዖንንም በተናገሩት ጊዜ ሙሴ የሰማንያ ዓመት ሰው ነበረ፥ አሮንም የሰማንያ ሦስት ዓመት ሰው ነበረ።
- 8
እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ሲል ተናገራቸው።
- 9
ፈርዖን። ተአምራትን አሳዩኝ ሲላችሁ፥ አሮንን። በትርህን ወስደህ እባብ እንድትሆን በፈርዖን ፊት ጣላት በለው።
- 10
ሙሴና አሮንም ወደ ፈርዖን ገቡ፥ እግዚአብሔርም እንዳዘዛቸው እንዲሁ አደረጉ፤ አሮንም በትሩን በፈርዖንና በባሮቹ ፊት ጣለ፥ እባብም ሆነች።
- 11
ፈርዖንም ጠቢባንንና መተተኞችን ጠራ፤ የግብፅም ጠንቋዮች በአስማታቸው እንዲሁ ደግሞ አደረጉ።
- 12
እያንዳንዳቸውም በትራቸውን ጣሉ፥ እባቦችም ሆኑ፤ የአሮን በትር ግን በትራቸውን ዋጠች።
- 13
እግዚአብሔር እንደ ተናገረ፥ የፈርዖን ልብ ጸና፥ አልሰማቸውምም።
- 14
እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። የፈርዖን ልብ ደነደነ፥ ሕዝቡንም ለመልቀቅ እንቢ አለ።
- 15
ማልደህ ወደ ፈርዖን ሂድ፤ እነሆ ወደ ውኃ ይወጣል፥ ትገናኘውም ዘንድ አንተ በወንዝ ዳር ትቆማለህ፤ እባብም ሆና የተለወጠችውን በትር በእጅህ ትወስዳለህ።
- 16
እንዲህም ትለዋለህ። የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር። በምድረ በዳ እንዲያገለግሉኝ ሕዝቤን ልቀቅ ብሎ ወደ አንተ ላከኝ፤ እነሆም እስከ ዛሬ አልሰማህም።
- 17
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ በዚህ ታውቃለህ፤ እነሆ እኔ የወንዙን ውኃ በእጄ ባለችው በትር እመታለሁ፥ ውኃውም ተለውጦ ደም ይሆናል።
- 18
በወንዙም ያሉት ዓሦች ይሞታሉ፥ ወንዙም ይገማል፤ ግብፃውያንም የወንዙን ውኃ ለመጠጣት ይጠላሉ።
- 19
እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። አሮንን። በትርህን ውሰድ፥ ደምም እንዲሆኑ በግብፅ ውኆች በወንዞቻቸውም በመስኖቻቸውም በኩሬዎቻቸውም በውኃ ማከማቻዎቻቸውም ሁሉ ላይ እጅህን ዘርጋ በለው፤ በግብፅም አገር ሁሉ በእንጨት ዕቃና በድንጋይ ዕቃ ሁሉ ደም ይሆናል።
- 20
ሙሴና አሮንም እግዚአብሔር እንዳዘዛቸው እንዲሁ አደረጉ፤ በትሩንም አነሣ፥ በፈርዖንና በባሪያዎቹም ፊት የወንዙን ውኃ መታ፤ የወንዙም ውኃ ሁሉ ተለውጦ ደም ሆነ።
- 21
በወንዙም የነበሩ ዓሦች ሞቱ፤ ወንዙም ገማ፥ ግብፃውያንም ከወንዙ ውኃ ይጠጡ ዘንድ አልቻሉም ደሙም በግብፅ አገር ሁሉ ነበረ።
- 22
የግብፅም ጠንቋዮች በአስማታቸው እንዲሁ አደረጉ፤ እግዚአብሔርም እንደተናገረ የፈርዖን ልብ ጸና፥ አልሰማቸውምም።
- 23
ፈርዖንም ተመልሶ ወደ ቤቱ ገባ፥ ይህንም ደግሞ በልቡ አላኖረውም።
- 24
ግብፃውያንም ሁሉ የወንዙን ውኃ ይጠጡ ዘንድ አልቻሉምና በወንዙ አጠገብ ውኃ ሊጠጡ ቆፈሩ።
- 25
እግዚአብሔርም ወንዙን ከመታ በኋላ ሰባት ቀን ተፈጸመ።