Exodus 4
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
ሙሴም መለሰ። እነሆ አያምኑኝም ቃሌንም አይሰሙም። እግዚአብሔር ከቶ አልተገለጠልህም ይሉኛል አለ።
- 2
እግዚአብሔርም። ይህች በእጅህ ያለችው ምንድር ናት? አለው። እርሱም። በትር ናት አለ።
- 3
ወደ መሬት ጣላት አለው፤ እርሱም በመሬት ጣላት፥ እባብም ሆነች፤ ሙሴም ከእርሷ ሸሸ።
- 4
- 5
እግዚአብሔርም ሙሴን። የአባቶቻቸው አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ፥ እግዚአብሔር እንደ ተገለጠልህ እንዲያምኑ እጅህን ዘርግተህ ጅራትዋን ያዝ አለው። እጁንም ዘርግቶ ያዛት በእጁም ውስጥ በትር ሆነች።
- 6
እግዚአብሔርም ደግሞ። እጅህን ወደ ብብትህ አግባ አለው። እጁንም ወደ ብብቱ አገባት፤ ባወጣትም ጊዜ እነሆ፥ እጁ እንደ በረዶ ለምጽ ሆነች።
- 7
እርሱም። እጅህን ወደ ብብትህ መልስ አለው። እጁንም ወደ ብብቱ መለሳት፥ ከብብቱም ባወጣት ጊዜ እነሆ ተመልሳ ገላውን መሰለች።
- 8
ደግሞም አለው። እንዲህም ይሆናል፤ ባያምኑህ የፊተኛይቱንም ምልክት ነገር ባይሰሙ፥ የሁለተኛይቱን ምልክት ነገር ያምናሉ።
- 9
እንዲህም ይሆናል፤ እነዚህን ሁለት ምልክቶች ባያምኑ ቃልህንም ባይሰሙ፥ ከወንዙ ውኃን ውሰድ፥ በደረቁም መሬት ላይ አፍስሰው፤ ከወንዙም የወሰድኸው ውኃ በደረቁ መሬት ላይ ደም ይሆናል።
- 10
ሙሴም እግዚአብሔርን። ጌታ ሆይ፥ እኔ አፌ ኰልታፋ ምላሴም ጸያፍ የሆነ ሰው ነኝ፤ ትናንት ከትናንት ወዲያ ባሪያህንም ከተናገርኸኝ ጀምሮ አፈ ትብ ሰው አይደለሁም።
- 11
እግዚአብሔርም። የሰውን አፍ የፈጠረ ማን ነው? ዲዳስ ደንቆሮስ የሚያይስ ዕውርስ ያደረገ ማን ነው? እኔ እግዚአብሔር አይደለሁምን?
- 12
እንግዲህ አሁን ሂድ፥ እኔም ከአፍህ ጋር እሆናለሁ፥ የምትናገረውንም አስተምርሃለሁ አለው።
- 13
እርሱም። ጌታ ሆይ፥ በምትልከው ሰው እጅ ትልክ ዘንድ እለምንሃለሁ አለ።
- 14
የእግዚአብሔርም ቍጣ በሙሴ ላይ ነደደ እንዲህም አለ። ሌዋዊው ወንድምህ አሮን አለ አይደለምን? እርሱ ደህና እንዲናገር አውቃለሁ፤ እነሆም ደግሞ ሊገናኝህ ይመጣል፤ ባየህም ጊዜ በልቡ ደስ ይለዋል።
- 15
አንተም ትናገረዋለህ ቃሉንም በአፉ ታደርገዋለህ፤ እኔ ከአፍህና ከአፉ ጋር እሆናለሁ፥ የምታደርጉትንም አስተምራችኋለሁ።
- 16
እርሱ ስለ አንተ ከሕዝቡ ጋር ይናገራል፤ እንዲህም ይሆናል፤ እርሱ አፍ ይሆንልሃል አንተም በእግዚአብሔር ፋንታ ትሆንለታለህ።
- 17
ይህችንም ተአምራት የምታደርግባትን በትር በእጅህ ይዘሃት ሂድ።
- 18
ሙሴም ሄደ፥ ወደ አማቱ ወደ ዮቶር ተመለሰ። እስከ ዛሬ በሕይወት እንዳሉ አይ ዘንድ ተመልሼ ወደ ግብፅ ወደ ወንድሞቼ ልሂድ አለው። ዮቶርም ሙሴን። በሰላም ሂድ አለው።
- 19
እግዚአብሔርም ሙሴን በምድያም። ነፍስህን የሚሹአት ሰዎች ሁሉ ሞተዋልና ተመልሰህ ወደ ግብፅ ሂድ አለው።
- 20
ሙሴም ሚስቱንና ልጆቹን ወሰደ፥ በአህያ ላይም አስቀመጣቸው፥ ወደ ግብፅም አገር ተመለሰ፤ ሙሴም የእግዚአብሔርን በትር ይዞ ሄደ።
- 21
እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። ወደ ግብፅ ስትመለስ በእጅህ ያደረግሁትን ተአምራት ሁሉ በፈርዖን ፊት ታደርገው ዘንድ ተመልከት፤ እኔ ግን ልቡን አጸናዋለሁ፥ ሕዝቡንም አይለቅቅም።
- 22
ፈርዖንንም። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል።
- 23
እስራኤል የበኵር ልጄ ነው፤ ይገዛልኝ ዘንድ ልጄን ልቀቅ አልሁህ፤ አንተም ትለቅቀው ዘንድ እንቢ አልህ፤ እነሆ እኔ የበኵር ልጅህን እገድላለሁ ትለዋለህ።
- 24
እንዲህም ሆነ፤ በመንገድ ላይ ባደረበት ስፍራ እግዚአብሔር ተገናኘው፥ ሊገድለውም ፈለገ።
- 25
ሲፓራም ሚስቱ ባልጩት ወሰደች፥ የልጅዋንም ሸለፈት ገረዘች፥ ወደ እግሩም ጣለችው። አንተ ለእኔ የደም ሙሽራ ነህ አለች።
- 26
ከእርሱም ፈቀቅ አለ። የዚያን ጊዜ። ስለ ግርዛቱ አንተ የደም ሙሽራ ነህ አለች።
- 27
እግዚአብሔርም አሮንን። ሄደህ በምድረ በዳ ሙሴን ተገናኘው አለው፤ ሄዶም በእግዚአብሔር ተራራ ተገናኘው፥ ሳመውም።
- 28
ሙሴም እግዚአብሔር በእርሱ ዘንድ የላከውን ቃል ሁሉ ያዘዘውንም ተአምራት ሁሉ ለአሮን ተናገረው።
- 29
ሙሴና አሮንም ሄዱ የእስራኤልንም ልጆች ሽማግሌዎች ሁሉ ሰበሰቡ።
- 30
አሮንም እግዚአብሔር ለሙሴ የነገረውን ቃል ሁሉ ተናገረ፥ ተአምራቱንም በሕዝቡ ፊት አደረገ።
- 31
ሕዝቡም አመኑ፤ እግዚአብሔርም የእስራኤልን ልጆች እንደ ጐበኘ ጭንቀታቸውንም እንዳየ በሰሙ ጊዜ፥ አጐነበሱ ሰገዱም።