Proverbs 26
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
በረዶ በበጋ ዝናብም በመከር እንዳይገባ፥ እንዲሁ ለሰነፍ ክብር አይገባውም።
- 2
እንደሚተላለፍ ድንቢጥ ወዲያና ወዲህም እንደሚበርር ጨረባ፥ እንዲሁ ከንቱ እርግማን በማንም ላይ አይደርስም።
- 3
አለንጋ ለፈረስ፥ ልጓም ለአህያ፥ በትርም ለሰነፍ ጀርባ ነው።
- 4
አንተ ደግሞ እርሱን እንዳትመስል ለሰነፍ እንደ ስንፍናው አትመልስለት።
- 5
ለራሱ ጠቢብ የሆነ እንዳይመስለው ለሰነፍ እንደ ስንፍናው መልስለት።
- 6
በሰነፍ መልእክተኛ እጅ ነገርን የሚልክ እግሮቹን ይቈርጣል ግፍንም ይጠጣል።
- 7
እንደሚንጠለጠሉ የአንካሳ እግሮች፥ እንዲሁም ምሳሌ በሰነፎች አፍ ነው።
- 8
ለሰነፍ ክብርን የሚሰጥ ድንጋይን በወንጭፍ እንደሚያስር ነው።
- 9
እሾህ በስካር እጅ እንደሚሰካ፥ እንዲሁ ምሳሌ በሰነፎች አፍ ነው።
- 10
ዋና ሠራተኛ ሁሉን ነገር ይሠራል፤ ሰነፍን የሚቀጥር ግን መንገድ አላፊውን እንደሚቀጥር ነው።
- 11
ወደ ትፋቱ እንደሚመለስ ውሻ ስንፍናውን የሚደግም ሰው እንዲሁ ነው።
- 12
ለራሱ ጠቢብ የሆነ የሚምስለውን ሰው አየኽውን? ከእርሱ ይልቅ ለሰነፍ ተስፋ አለው።
- 13
ታካች ሰው። አንበሳ በመንገድ አለ፤ አንበሳ በጎዳና አለ ይላል።
- 14
ሣንቃ በማጠፊያው ላይ እንደሚዞር፥ እንዲሁ ታካች ሰው በአልጋው ላይ ይመላለሳል።
- 15
ታካች ሰው እጁን ወደ ወጭት ያጠልቃል፤ ወደ አፉም ይመልሳት ዘንድ ለእርሱ ድካም ነው።
- 16
ታካች ሰው በጥበብ ከሚመልሱ ከሰባት ሰዎች ይልቅ ለራሱ ጠቢብ የሆነ ይመስለዋል።
- 17
አልፎ በሌላው ጥል የሚደባለቅ ውሻን በጅራቱ እንደሚይዝ ነው።
- 18
ትንታግንና ፍላጻን ሞትንም እንደሚወረውር እንደ ዕብድ ሰው፥
- 19
ባልንጀራውን የሚያታልል። በጨዋታ አደረግሁት የሚል ሰውም እንዲሁ ነው።
- 20
እንጨት ባለቀ ጊዜ እሳት ይጠፋል፤ ጆሮ ጠቢ በሌለበትም ዘንድ ጠብ ጸጥ ይላል።
- 21
ከሰል ፍምን እንጨትም እሳትን እንዲያበዛ፥ እንዲሁ ቍጡ ሰው ጠብን ያበዛል።
- 22
የጆሮ ጠቢ ቃል እንደ ጣፋጭ መብል ነው፥ እርሱም እስከ ሆድ ጕርጆች ድረስ ይወርዳል።
- 23
ክፋት በልቡ ሳለ ፍቅርን የሚናገር ከንፈር በብር ዝገት እንደ ተለበጠ የሸክላ ዕቅ ነው።
- 24
ጠላት በከንፈሩ ተስፋ ይሰጣል፥ በልቡ ግን ተንኰልን ያኖራል።
- 25
በልቡ ሰባት ርኵሰት አለበትና በቃሉ አሳምሮ ቢናገርህ አትመነው።
- 26
ጠላትነቱን በተንኰል የሚሸሽግ፥ ክፋቱ በጉባኤ መካከል ይገለጣል።
- 27
ጕድጓድን የሚምስ ይወድቅበታል፤ ድንጋይንም የሚያንከባልል ይገለበጥበታል።
- 28
ሐሰተኛ ምላስ ያቈሰላቸውን ሰዎች ይጠላል፤ ልዝብ አፍም ጥፋትን ያመጣል።