Proverbs 25
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
እነዚህም ደግሞ የይሁዳ ንጉሥ የሕዝቅያስ ሰዎች የቀዱአቸው የሰሎሞን ምሳሌዎች ናቸው።
- 2
የእግዚአብሔር ክብር ነገርን መሰወር ነው፤ የነገሥታት ክብር ግን ነገርን መመርመር ነው።
- 3
እንደ ሰማይ ከፍታ እንደ ምድርም ጥልቀት የነገሥታት ልብ አይመረመርም።
- 4
ከብር ዝገትን አስወግድ፥ ፈጽሞም ይጠራል።
- 5
ከንጉሥ ፊት ኀጥኣንን አርቅ፥ ዙፋኑም በጽድቅ ትጸናለች።
- 6
በንጉሥ ፊት አትመካ፥ በታላልቆችም ስፍራ አትቁም፤
- 7
ዓይኖችህ ባዩት በመኰንን ፊት ከምትዋረድ። ወደዚህ ከፍ በል ብትባል ይሻልሃልና።
- 8
ባልንጀራህ ባሳፈረህ ጊዜ ኋላ እንዳትጸጸት ለክርክር ፈጥነህ አትውጣ፤
- 9
ክርክርህን ከባልንጀራህ ጋር ተከራከር፤ የሌላ ሰው ምሥጢር ግን አትግለጥ፥
- 10
የሚሰማ እንዳይነቅፍህ፥ አንተንም ከማነወር ዝም እንዳይል።
- 11
የወርቅ እንኮይ በብር ፃሕል ላይ፤ የጊዜው ቃል እንዲሁ ነው።
- 12
የምትሰማን ጆሮ የሚዘልፍ ጠቢብ ሰው እንደ ወርቅ ጉትቻ እንደሚያንጸባርቅም ዕንቍ እንዲሁ ነው።
- 13
በመከር ወራት የውርጭ ጠል ደስ እንደሚያሰኝ፥ እንዲሁ የታመነ መልእክተኛ ለላኩት ነው፤ የጌቶቹን ነፍስ ያሳርፋልና።
- 14
ስለ ስጦታው በሐሰት የሚመካ ሰው ዝናብ እንደማይከተለው ደመና ነፋስም ነው።
- 15
በትዕግሥት አለቃ ይለዝባል፥ የገራም ምላስ አጥንትን ይሰብራል።
- 16
አጥብቀህ እንዳትጠግብ እንዳትተፋውም ማር ባገኘህ ጊዜ የሚበቃህን ብላ።
- 17
እንዳይሰለችህ እንዳይጠላህም እግርህን ወደ ባልንጀራህ ቤት አታዘውትር።
- 18
በባልንጀራው በሐሰት የሚመሰክር እንደ መዶሻና እንደ ሰይፍ እንደ ተሳለም ፍላጻ ነው።
- 19
ወስላታውን ሰው በመከራ ጊዜ መተማመን እንደ ተሰበረ ጥርስና እንደ ሰለለ እግር ነው።
- 20
ለሚያዝን ልብ ዝማሬ የሚዘምር፥ ለብርድ ቀን መጐናጸፊያውን እንደሚያስወግድ በቍስልም ላይ እንደ መጻጻ እንዲሁ ነው።
- 21
ጠላትህ ቢራብ እንጀራ አብላው፥ ቢጠማም ውኃ አጠጣው፤
- 22
ፍም በራሱ ላይ ትሰበስባለህና፥ እግዚአብሔርም ዋጋህን ይመልስልሃልና።
- 23
የሰሜን ነፋስ ወጀብ ያመጣል፤ ሐሜተኛ ምላስም የሰውን ፊት ያስቈጣል።
- 24
ከጠበኛ ሴት ጋር በአንድ ቤት ከመቀመጥ በሰገነት ማዕዘን መቀመጥ ይሻላል።
- 25
የቀዘቀዘ ውኃ ለተጠማች ነፍስ ደስ እንደሚያሰኝ፥ ከሩቅ አገር የመጣ መልካም ምስራች እንዲሁ ነው።
- 26
በኀጥእ ፊት የሚወድቅ ጻድቅ እንደደፈረሰ ፈሳሽና እንደ ረከሰ ምንጭ ነው።
- 27
ብዙ ማር መብላት መልካም አይደለም፤ እንዲሁም የራስን ክብር መፈላለግ አያስከብርም።
- 28
ቅጥር እንደሌላት እንደ ፈረሰች ከተማ፥ መንፈሱን የማይከለክል ሰው እንዲሁ ነው።