Numbers 34
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
- 2
የእስራኤልን ልጆች እንዲህ ብለህ እዘዛቸው። ወደ ከነዓን ምድር በገባችሁ ጊዜ፥ ርስት ትሆናችሁ ዘንድ በዕጣ የምትደርሳችሁ ምድር፥ በዳርቻዋ ያለች የከነዓን ምድር፥
- 3
ይህች ናት፤ የደቡቡ ወገን ከጺን ምድረ በዳ በኤዶምያስ በኩል ይሆናል፤ የደቡቡም ዳርቻ ከጨው ባሕር ዳር በምሥራቅ በኩል ይጀምራል፤
- 4
ዳርቻችሁም በአቅረቢም ዐቀበት በደቡብ በኩል ይዞራል ወደ ጺንም ያልፋል፤ መውጫውም በቃዴስ በርኔ በደቡብ በኩል ይሆናል፤ ወደ ሐጸርአዳር ይሄዳል ወደ ዓጽሞንም ያልፋል፤
- 5
ዳርቻውም ከዓጽሞን ወደ ግብፅ ወንዝ ይዞራል፥ መውጫውም በባሕሩ በኩል ይሆናል።
- 6
ለምዕራብም ዳርቻ ታላቁ ባሕር ዳርቻችሁ ይሆናል፤ ይህ የምዕራብ ዳርቻችሁ ይሆናል።
- 7
የሰሜንም ዳርቻችሁ ይህ ይሆናል፤ ከታላቁ ባሕር ወደ ሖር ተራራ ምልክት ታመለክታላችሁ፤
- 8
ከሖርም ተራራ ወደ ሐማት መግቢያ ምልክት ታመለክታላችሁ የዳርቻውም መውጫ በጽዳድ ይሆናል፤
- 9
ዳርቻውም ወደ ዚፍሮን ያልፋል እስከ ሐጸርዔናንም ድረስ ይወጣል፤ ይህ የሰሜን ዳርቻችሁ ይሆናል።
- 10
የምሥራቁንም ዳርቻችሁን ከሐጸርዔናን ወደ ሴፋማ ምልክት ታመለክታላችሁ፤
- 11
ዳርቻውም ከሴፋማ በዓይን ምሥራቅ ወዳለው ወደ ሪብላ ይወርዳል፤ እስከ ኪኔሬት የባሕር ወሽመጥ በምሥራቅ በኩል ይደርሳል፤
- 12
ዳርቻውም ወደ ዮርዳኖስ ይወርዳል፥ መውጫውም በጨው ባሕር ይሆናል። ምድራችሁ እንደ ዳርቻዋ በዙሪያዋ ይህች ናት።
- 13
ሙሴም የእስራኤልን ልጆች እንዲህ ብሎ አዘዛቸው። እግዚአብሔር ለዘጠኝ ነገድ ተኩል ይሰጡአቸው ዘንድ ያዘዘ በዕጣ የምትወርሱአት ምድር ይህች ናት፤
- 14
የሮቤልም ልጆች ነገድ በየአባቶቻቸው ቤት፥ የጋድም ልጆች ነገድ በየአባቶቻቸው ቤት፥ የምናሴም ነገድ እኩሌታ ርስታቸውን ወርሰዋል።
- 15
እነዚህ ሁለቱ ነገድና የአንዱ ነገድ እኩሌታ ርስታቸውን በዮርዳኖስ ማዶ በኢያሪኮ አንጻር በምሥራቅ በኩል ወረሱ።
- 16
እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
- 17
ምድሪቱን ርስት አድርገው የሚከፍሉላችሁ ሰዎች ስማቸው ይህ ነው፤ ካህኑ አልዓዛርና የነዌ ልጅ ኢያሱ።
- 18
ምድሪቱንም ርስት አድርገው ይከፍሉ ዘንድ ከየነገዱ አንድ አንድ አለቃ ትወስዳላችሁ።
- 19
የሰዎቹም ስም ይህ ነው፤ ከይሁዳ ነገድ የዮፎኒ ልጅ ካሌብ፥
- 20
ከስምዖን ልጆች ነገድ የዓሚሁድ ልጅ ሰላሚኤል፥
- 21
ከብንያም ነገድ የኪስሎን ልጅ ኤልዳድ፥
- 22
ከዳን ልጆች ንገድ አንድ አለቃ የዮግሊ ልጅ ቡቂ፥
- 23
ከዮሴፍም ልጆች ከምናሴ ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የሱፊድ ልጅ አኒኤል፥
- 24
ከኤፍሬም ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የሺፍጣን ልጅ ቀሙኤል፥
- 25
ከዛብሎን ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የፈርናክ ልጅ ኤሊሳፈን፥
- 26
ከይሳኮር ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የሖዛ ልጅ ፈልጢኤል፥
- 27
ከአሴር ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የሴሌሚ ልጅ አሒሁድ፥
- 28
ከንፍታሌም ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የዓሚሁድ ልጅ ፈዳሄል።
- 29
እግዚአብሔር በከነዓን ምድር ለእስራኤል ልጆች ርስታቸውን ይከፍሉ ዘንድ ያዘዛቸው እነዚህ ናቸው።