Job 6
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
ኢዮብም መለሰ እንዲህም አለ።
- 2
ትካዜዬ ምነው በተመዘነ ኖሮ! መከራዬም ሁሉ ምነው በሚዛን ላይ በተደረገ ኖሮ!
- 3
ከባሕር አሸዋ ይልቅ ይከብድ ነበርና፤ ስለዚህ ቃሌ ደፋር ሆኖአል።
- 4
ሁሉን የሚችል የአምላክ ፍላጻ በሥጋዬ ውስጥ ነው፥ መርዙንም ነፍሴ ትጠጣለች፤ የእግዚአብሔር ድንጋጤ በላዬ ተሰልፎአል።
- 5
በውኑ የሜዳ አህያ ሣር ሳለው ይጮኻልን? ወይስ በሬ ገለባ ሳለው ይጮኻልን?
- 6
የማይጣፍጥስ ነገር ያለ ጨው ይበላልን? ወይስ የእንቁላል ውኃ ይጥማልን?
- 7
ሰውነቴ ትነካው ዘንድ እንቢ አለችው፤ እንደሚያስጸይፍ መብል ሆነብኝ።
- 8
ልመናዬ ምነው በደረሰልኝ! እግዚአብሔርም ምኞቴን ምነው በሰጠኝ!
- 9
እግዚአብሔርም ያደቀኝ ዘንድ እጁንም ለቅቆ ያጠፋኝ ዘንድ ወድዶ ቢሆን ኖሮ!
- 10
መጽናናት በሆነልኝ ነበር፤ በማይራራ ሕመም ሐሤት ባደረግሁ ነበር፥ የቅዱሱን ቃል አልካድሁምና።
- 11
እጠብቅ ዘንድ ጕልበቴ ምንድር ነው? እታገሥም ዘንድ ፍጻሜዬ ምንድር ነው?
- 12
ጕልበቴ የድንጋይ ጕልበት ነውን? ሥጋዬስ እንደ ናስ ነውን?
- 13
በውኑ ረድኤት በእኔ እንደሌለ ጥበብም ሁሉ ከእኔ ዘንድ እንደ ተባረረ አይደለምን?
- 14
ሁሉን የሚችለውን የአምላክን መፍራት ለሚተው፥ ለመዛል ለቀረበው ስንኳ ወዳጁ ቸርነትን ሊያሳይ ይገባል።
- 15
ወንድሞቼ እንደ ፈፋ፥ እንደሚያልፍ ፈፋ ሐሰተኞች ሆኑብኝ።
- 16
ከበረዶ የተነሣ ደፈረሱ፥ አመዳይም ተሰወረባቸው፤
- 17
ፀሐይ በተኰሰች ጊዜ ይደርቃሉ፤ በሙቀትም ጊዜ ከስፍራቸው ይጠፋሉ።
- 18
በየዳርቻቸውም የሚሄዱ ነጋዴዎች ፈቀቅ ይላሉ፤ ወደ በረሃ ወጥተው ይጠፋሉ።
- 19
የቴማን ነጋዴዎች ተመለከቱ፥ የሳባ መንገደኞችም ተጠባበቁአቸው።
- 20
ተስፋ አድርገዋቸው ነበርና አፈሩ፤ ወደዚያ ደረሱ፥ እፍረትም ያዛቸው።
- 21
አሁንም እናንተ እንደዚሁ ሆናችኋል፤ መከራዬን አይታችሁ ፈራችሁ።
- 22
በውኑ። አንዳች ነገር አምጡልኝ፤ ወይስ። ከብልጥግናችሁ ስጦታ አቅርቡልኝ፤
- 23
ወይስ። ከጠላቴ እጅ አስጥሉኝ፤ ወይስ። ከአስጨናቂው እጅ አድኑኝ አልኋችሁን?
- 24
አስተምሩኝ፥ እኔም ዝም እላለሁ፤ የተሳሳትሁትንም ንገሩኝ።
- 25
የቅንነት ቃል እንዴት ኃይለኛ ነው! የእናንተ ሙግት ግን ምን ይገሥጻል?
- 26
ተስፋ የሌለው ሰው ንግግር እንደ ነፋስ ነውና ቃሌን ትገሥጹ ዘንድ ታስባላችሁን?
- 27
በድሀ አደጉ ላይ ዕጣ ትጣጣላላችሁ፤ ለወዳጆቻችሁም ጕድጓድ ትቈፍራላችሁ።
- 28
አሁንም፥ እባካችሁ፥ ወደ እኔ ተመልከቱ፤ በፊታችሁም ሐሰት አልናገርም።
- 29
እባካችሁ፥ ተመለሱ፤ በደል አይሁን፤ ጽድቄ በዚህ ነገር ነውና አንድ ጊዜ ተመለሱ።
- 30
በውኑ በአንደበቴ በደል ይገኛልን? አፌስ ተንኰልን ይለይ ዘንድ አይችልምን?