Job 5
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
አሁንም ጥራ፤ የሚመልስልህ አለን? ከቅዱሳንስ ወደማናቸው ትዞራለህ?
- 2
ሰነፉን ሰው ቍጣ ይገድለዋል፥ ሰነፉንም ቅንዓት ያጠፋዋል።
- 3
ሰነፍ ሰው ሥር ሰድዶ አየሁት፥ ድንገትም መኖሪያውን ረገምሁ።
- 4
ልጆቹም ከደኅንነት ርቀዋል፥ በበርም ውስጥ ተረግጠዋል፥ የሚታደጋቸውም የለም።
- 5
የሰበሰበውንም ራብተኛ ይበላዋል፥ ከእሾህም ውስጥ እንኳ ያወጣዋል፤ የተጠማ ሀብታቸውን ዋጠ።
- 6
ችግር ከትቢያ አይመጣም፥ መከራም ከመሬት አይበቅልም፤
- 7
የአሞራ ግልገሎች ግን ወደ ላይ እየበረሩ ከፍ እንዲሉ፥ ሰው እንዲሁ ለመከራ ተወልዶአል።
- 8
እኔ ግን እግዚአብሔርን እለምን ነበር፥ ነገሬንም ወደ እግዚአብሔር አቀርብ ነበር።
- 9
የማይመረመረውን ታላቅ ነገርና የማይቈጠረውን ተአምራት ያደርጋል።
- 10
በምድር ላይ ዝናብን ይሰጣል፥ በእርሻም ላይ ውኃ ይልካል።
- 11
የተዋረዱትን ወደ ላይ ያወጣል፥ ኀዘንተኞችንም ለደኅንነት ከፍ ከፍ ያደርጋቸዋል።
- 12
እጃቸውም ምክራቸውን እንዳይፈጽም የተንኰለኞችን አሳብ ከንቱ ያደርገዋል።
- 13
ጠቢባንን በተንኰላቸው ይይዛቸዋል፤ የጠማሞችንም ምክር ይዘረዝራል።
- 14
በቀን ጨለማን ያገኛሉ፥ በቀትርም ጊዜ በሌሊት እንዳሉ ይርመሰመሳሉ።
- 15
ድሀውንም ከአፋቸው ሰይፍ ከኃያሉም እጅ ያድነዋል።
- 16
ለምስኪኑም ተስፋ አለው፤ ክፋት ግን አፍዋን ትዘጋለች።
- 17
እነሆ፥ እግዚአብሔር የሚገሥጸው ሰው ምስጉን ነው፤ ስለዚህ ሁሉን የሚችለውን የአምላክን ተግሣጽ አትናቅ።
- 18
እርሱ ይሰብራል፥ ይጠግንማል፤ ያቈስላል፥ እጆቹም ይፈውሳሉ።
- 19
በስድስት ክፉ ነገር ውስጥ ያድንሃል፥ በሰባትም ውስጥ ክፋት አትነካህም።
- 20
በራብ ጊዜ ከሞት፥ በሰልፍም ከሰይፍ እጅ ያድንሃል።
- 21
ከምላስ ጅራፍ ትሰወራለህ፤ ጥፋትም ሲመጣ አትፈራም።
- 22
በጥፋትና በራብ ላይ ትስቃለህ፤ ከምድረ በዳ አራዊትም አትፈራም፤
- 23
ቃል ኪዳንህ ከምድረ በዳ ድንጋይ ጋር ይሆናልና፤ የምድረ በዳም አራዊት ከአንተ ጋር ይስማማሉና።
- 24
ድንኳንህም በሰላም እንዲሆን ታውቃለህ፤ በረትህን ትጐበኛለህ አንዳችም አይጐድልብህም።
- 25
ዘርህም ታላቅ እንዲሆን፥ ትውልድህም እንደ ምድር ሣር እንዲሆን ታውቃለህ።
- 26
በወራቱ የእህሉ ነዶ ወደ አውድማ እንዲገባ፥ በረጅም ዕድሜ ወደ መቃብር ትገባለህ።
- 27
እነሆ፥ ይህችን መረመርን፥ የሰማነውም ይህ ነው፤ አንተ ግን አንዳች ሠርተህ እንደ ሆነ ለራስህ እወቀው።