Jeremiah 38
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
ኤርምያስም ለሕዝቡ ሁሉ የተናገረውን ቃል የማታን ልጅ ስፋጥያስ፥ የጳስኮርም ልጅ ጎዶልያስ፥ የሰሌምያም ልጅ ዮካል፥ የመልክያም ልጅ ጳስኮር ሰሙ።
- 2
ኤርምያስ እንዲህ ብሎአልና። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በዚህች ከተማ የሚቀመጥ በሰይፍና በራብ በቸነፈርም ይሞታል፤ ወደ ከለዳውያን ግን የሚወጣ በሕይወት ይኖራል፥ ነፍሱም እንደ ምርኮ ትሆንለታለች፥ በሕይወትም ይኖራል።
- 3
እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። ይህች ከተማ በባቢሎን ንጉሥ ሠራዊት እጅ በእርግጥ ትሰጣለች፥ እርሱም ይይዛታል።
- 4
አለቆቹም ንጉሡን። ይህን የመሰለውን ቃል ሲነግራቸው በዚህች ከተማ የቀሩትን የሰልፈኞቹን እጅ የሕዝቡንም ሁሉ እጅ ያደክማልና ይህ ሰው እንዲገደል እንለምንሃለን፤ ይህ ሰው ክፋትን እንጂ ለዚህ ሕዝብ ሰላምን አይመኝለትምና አሉት።
- 5
ንጉሡም ሴዴቅያስ። ንጉሡ በእናንተ ላይ ምንም ሊያደርግ አይችልምና እነሆ፥ በእጃችሁ ነው አለ።
- 6
ኤርምያስንም ወሰዱት በግዞት ቤቱም አደባባይ ወደ ነበረው ወደ ንጉሡ ልጅ ወደ መልክያ ጕድጓድ ውስጥ ጣሉት፤ ኤርምያስንም በገመድ አወረዱት። በጕድጓድም ውስጥ ጭቃ እንጂ ውኃ አልነበረበትም፤ ኤርምያስም ወደ ጭቃው ውስጥ ገባ።
- 7
በንጉሡም ቤት የነበረው ጃንደረባ ኢትዮጵያዊው አቤሜሌክ ኤርምያስን በጕድጓዱ ውስጥ እንዳኖሩት ሰማ። ንጉሡም በብንያም በር ተቀምጦ ነበር።
- 8
አቤሜሌክም ከንጉሡ ቤት ወጥቶ ንጉሡን እንዲህ አለው።
- 9
ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ እነዚህ ሰዎች ነቢዮን ኤርምያስን በጕድጓድ ውስጥ በመጣላቸው በእርሱ ላይ በማድረጋቸው ሁሉ ክፉ አድርገዋል፤ በከተማይቱም ውስጥ እንጀራ ስለሌለ በዚያ በራብ ይሞታል።
- 10
ንጉሡም ኢትዮጵያዊውን አቤሜሌክም። ከአንተ ጋር ሠላሳ ሰዎች ከዚህ ውሰድ፥ ነቢዩም ኤርምያስ ሳይሞት ከጕድጓድ አውጣው ብሎ አዘዘው።
- 11
አቤሜሌክም ከእርሱ ጋር ሰዎችን ይዞ ሄደ፥ ከቤተ መዛግብቱም በታች ወደ ነበረው ወደ ንጉሥ ቤት ገባ፥ ከዚያም አሮጌ ጨርቅና እላቂ ልብስ ወሰደ፥ ወደ ኤርምያስም ወደ ጉድጓድ ውስጥ በገመድ አወረደው።
- 12
ኢትዮጵያዊውም አቤሜሌክ ኤርምያስን። ይህን አሮጌ ጨርቅና እላቂውን ልብስ በብብትህ ከገመዱ በታች አድርግ አለው፤ ኤርምያስም እንዲሁ አደረገ።
- 13
ኤርምያስንም በገመዱ ጐተቱት ከጕድጓድም አወጡት፥ ኤርምያስም በግዞት ቤት አደባባይ ተቀመጠ።
- 14
ንጉሡም ሴዴቅያስ ልኮ በእግዚአብሔር ቤት ወደ ነበረው ወደ ሦስተኛው መግቢያ ወደ እርሱ ነቢዩን ኤርምያስን አስመጣው፤ ንጉሡም ኤርምያስን። አንዲት ነገር እጠይቅሃለሁ፤ ምንም አትሸሽገኝ አለው።
- 15
ኤርምያስም ሴዴቅያስን። ብነግርህ በውኑ አትገድለኝምን? ብመክርህም አትሰማኝም አለው።
- 16
ንጉሡም ሴዴቅያስ። ይህችን ነፍስ የፈጠረልን ሕያው እግዚአብሔርን! አልገድልህም፥ ነፍስህንም ለሚሹ ለእነዚህ ሰዎች እጅ አሳልፌ አልሰጥህም ብሎ በቈይታ ለኤርምያስ ማለ።
- 17
ኤርምያስም ሴዴቅያስን። የእስራኤል አምላክ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ወደ ባቢሎን ንጉሥ አለቆች ብትወጣ፥ ነፍስህ በሕይወት ትኖራለች ይህችም ከተማ በእሳት አትቃጠልም፤ አንተም ቤትህም በሕይወት ትኖራላችሁ።
- 18
ወደ ባቢሎን ንጉሥ አለቆች ባትወጣ ግን፥ ይህች ከተማ በከለዳውያን እጅ ትሰጣለች፥ በእሳትም ያቃጥሉአታል አንተም ከእጃቸው አታመልጥም አለው።
- 19
ንጉሡም ሴዴቅያስ ኤርምያስን። ወደ ከለዳውያን በኰበለሉት በአይሁድ እጅ አሳልፈው ይሰጡኛል እነርሱም ያፌዙብኛል ብዬ እፈራለሁ አለው።
- 20
ኤርምያስም እንዲህ አለው። አሳልፈው አይሰጡህም። እኔ የምነግርህን የእግዚአብሔርን ቃል እባክህ፥ ስማ፤ ይቀናሃል ነፍስህም በሕይወት ትኖራለች።
- 21
ትወጣ ዘንድ እንቢ ብትል ግን፥ እግዚአብሔር ያሳየኝ ቃል ይህ ነው።
- 22
እነሆ፥ በይሁዳ ንጉሥ ቤት የቀሩትን ሴቶች ሁሉ ወደ ባቢሎን ንጉሥ አለቆች ያወጣሉ፤ እነዚያም ሴቶች። ባለምዋሎችህ አታልለውሃል አሸንፈውህማል፤ እግሮችህ ግን አሁን በጭቃ ውስጥ ከገቡ እነርሱ ከአንተ ወደ ኋላ ተመልሰዋል ይላሉ።
- 23
ሚስቶችህንና ልጆችህንም ሁሉ ወደ ከለዳውያን ያወጣሉ፤ አንተም በባቢሎን ንጉሥ እጅ ትያዛለህ እንጂ ከእጃቸው አታመልጥም፤ ይህችም ከተማ በእሳት ትቃጠላለች።
- 24
ሴዴቅያስም ኤርምያስን እንዲህ አለው። ይህም ቃል ማንም አይወቅ፥ አንተም አትሞትም።
- 25
አለቆቹ ግን እኔ ከአንተ ጋር እንደ ተነጋገርሁ ቢሰሙ፥ ወደ አንተም መጥተው። ለንጉሡ ያልኸውን ንገረን አትሸሽገንም፥ እኛም አንገድልህም፤ ደግሞ ንጉሡ ያለህን ንገረን ቢሉህ፥ አንተ።
- 26
በዚያ እሞት ዘንድ ወደ ዮናታን ቤት አትመልሰኝ ብዬ በንጉሡ ፊት ለመንሁ በላቸው።
- 27
አለቆቹም ሁሉ ወደ ኤርምያስ መጥተው ጠየቁ፥ ንጉሡም እንዳዘዘው እንደዚህ ቃል ሁሉ ነገራቸው። ነገሩም አልተሰማምና ከእርሱ ጋር መነጋገርን ተው።
- 28
ኢየሩሳሌም እስከ ተያዘችበት ቀን ድረስ በግዞት ቤት አደባባይ ተቀመጠ።