Jeremiah 37
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
የባቢሎንም ንጉሥ ናቡከደነፆር በይሁዳ ያነገሠው የኢዮስያስ ልጅ ሴዴቅያስ በኢዮአቄም ልጅ በኢኮንያን ፋንታ ነገሠ።
- 2
እርሱም ሆነ ባሪያዎቹ የአገሩም ሕዝብ በነቢዩ በኤርምያስ እጅ የተናገረውን የእግዚአብሔርን ቃል አልሰሙም።
- 3
ንጉሡም ሴዴቅያስ። ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ስለ እኛ ጸልይ ብሎ የሰሌምያን ልጅ ዮካልንና ካህኑን የመዕሤያን ልጅ ሶፎንያስን ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ ላከ።
- 4
እርሱንም በግዞት ቤት ገና አላገቡትም ነበርና ኤርምያስ በሕዝቡ መካከል ይወጣና ይገባ ነበር።
- 5
የፈርዖንም ሠራዊት ከግብጽ ወጣ፤ ኢየሩሳሌምንም ከብበዋት የነበሩ ከለዳውያን ይህን ወሬ በሰሙ ጊዜ ከኢየሩሳሌም ተመለሱ።
- 6
የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ።
- 7
የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ከእኔ ትጠይቁ ዘንድ የላካችሁን የይሁዳን ንጉሥ እንዲህ በሉት። እነሆ፥ ሊረዳችሁ የወጣው የፈርዖን ሠራዊት ወደ አገሩ ወደ ግብጽ ይመለሳል።
- 8
ከለዳውያንም ተመልሰው ይህችን ከተማ ይዋጉአታል ይይዙአትማል በእሳትም ያቃጥሉአታል።
- 9
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። አይሄዱምና። ከለዳውያን በእርግጥ ከእኛ ዘንድ ይሄዳሉ ብላችሁ ራሳችሁን አታታልሉ።
- 10
እናንተም የሚዋጉትን የከለዳውያንን ሠራዊት ሁሉ ብትመቱት ኖሮ፥ ከእነርሱም የተወጉት ብቻ ቢቀሩ ኖሮ፥ ሁሉ እያንዳንዱ በድንኳኑ ተነሥቶ ይህችን ከተማ በእሳት ባቃጠሉአት ነበር።
- 11
የከለዳውያንም ሠራዊት ከፈርዖን ሠራዊት ፊት የተነሣ ከኢየሩሳሌም በተመለሰ ጊዜ፥
- 12
ኤርምያስ በሕዝቡ መካከል የርስቱን እድል ፈንታ ከዚያ ይቀበል ዘንድ ወደ ብንያም አገር ሊሄድ ከኢየሩሳሌም ወጣ።
- 13
በብንያምም በር በነበረ ጊዜ የሐናንያ ልጅ የሰሌምያ ልጅ የሪያ የተባለ የዘበኞች አለቃ በዚያ ነበረ፤ እርሱም። ወደ ከለዳውያን መኰብለልህ ነው ብሎ ነቢዩን ኤርምያስን ያዘው።
- 14
ኤርምያስም። ሐሰት ነው፤ ወደ ከለዳውያን መኰብለሌ አይደለም አለ፤ እርሱ ግን አልሰማውም፥ የሪያም ኤርምያስን ይዞ ወደ አለቆች አመጣው።
- 15
አለቆችም ተቈጥተው ኤርምያስን መቱት፥ የጸሐፊውንም የዮናታንን ቤት የግዞት ቤት አድርገውት ነበርና በዚያ አኖሩት።
- 16
ኤርምያስም ወደ ጕድጓድ ቤት ወደ ጓዳዎቹ ገባ፤ ኤርምያስም በዚያ ብዙ ቀን ከተቀመጠ በኋላ፥
- 17
ንጉሡ ሴዴቅያስ ልኮ አስመጣው፥ ንጉሡም በቤቱ። በውኑ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሆነ ቃል አለን? ብሎ በቈይታ ጠየቀው። ኤርምያስም። አዎን አለ። ደግሞም። በባቢሎን ንጉሥ እጅ አልፈህ ትሰጣለህ አለ።
- 18
ኤርምያስም ደግሞ ንጉሡን ሴዴቅያስን እንዲህ አለው። በግዞት ቤት የጣላችሁኝ አንተን ወይስ ባሪያዎችህን ወይስ ሕዝብህን ምን በድያችሁ ነው?
- 19
የባቢሎን ንጉሥ በእናንተና በዚህች አገር አይመጣባችሁም ብለው ትንቢት ይናገሩላችሁ የነበሩ ነቢያቶቻችሁ ወዴት አሉ?
- 20
ንጉሡ ጌታዬ ሆይ፥ እንድትሰማኝ አሁን እለምንሃለሁ፤ እባክህ፥ ልመናዬ ወደ አንተ ይድረስ፤ በዚያ እንዳልሞት ወደ ጸሐፊው ወደ ዮናታን ቤት አትመልሰኝ።
- 21
ንጉሡም ሴዴቅያስ አዘዘ፥ ኤርምያስንም በግዞት ቤት አደባባይ አኖሩት፥ እንጀራም ሁሉ ከከተማ እስኪጠፋ ድረስ ዕለት ዕለት አንድ አንድ እንጀራ ከጋጋሪዎች መንገድ ይሰጡት ነበር። እንዲሁም ኤርምያስ በግዞት ቤት አደባባይ ተቀምጦ ነበር።