1 Samuel 16
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
እግዚአብሔርም ሳሙኤልን። በእስራኤል ላይ እንዳይነግሥ ለናቅሁት ለሳኦል የምታለቅስለት እስከ መቼ ነው? በቀንድህ ዘይቱን ሞልተህ ሂድ፤ በልጆቹ መካከል ንጉሥ አዘጋጅቻለሁና ወደ እሴይ ወደ ቤተ ልሔም እልክሃለሁ አለው።
- 2
ሳሙኤልም። እንዴት እሄዳለሁ? ሳኦል ቢሰማ ይገድለኛል አለ። እግዚአብሔርም። አንዲት ጊደር ይዘህ ሂድና፥ ለእግዚአብሔር እሠዋ ዘንድ መጣሁ በል።
- 3
እሴይንም ወደ መሥዋዕቱ ጥራው፥ የምታደርገውንም አስታውቅሃለሁ፤ የምነግርህንም ቅባልኝ አለው።
- 4
ሳሙኤልም እግዚአብሔር የተናገረውን አደረገ፥ ወደ ቤተ ልሔምም መጣ። የአገሩም ሽማግሌዎች እየተንቀጠቀጡ ሊገናኙት መጡና። የመጣኸው ለደኅንነት ነውን? አሉት።
- 5
እርሱም። ለደኅንነት ነው፤ ለእግዚአብሔር እሠዋ ዘንድ መጣሁ፤ ቅዱሳን ሁኑ፥ ከእኔም ጋር ወደ መሥዋዕቱ ኑ አለ። እሴይንና ልጆቹንም ቀደሳቸው፥ ወደ መሥዋዕቱም ጠራቸው።
- 6
እንዲህም ሆነ፤ በመጡ ጊዜ ወደ ኤልያብ ተመልክቶ። በእውነት እግዚአብሔር የሚቀባው በፊቱ ነው አለ።
- 7
እግዚአብሔር ግን ሳሙኤልን። ፊቱን የቁመቱንም ዘለግታ አትይ፤ ሰው እንዲያይ እግዚአብሔር አያይምና ናቅሁት፤ ሰው ፊትን ያያል፥ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል አለው።
- 8
እሴይም አሚናዳብን ጠርቶ በሳሙኤል ፊት አሳለፈው፤ እርሱም። ይህን ደግሞ እግዚአብሔር አልመረጠውም አለ።
- 9
እሴይም ሣማን አሳለፈው፤ እርሱም። ይህን ደግሞ እግዚአብሔር አልመረጠውም አለ።
- 10
እሴይም ከልጆቹ ሰባቱን በሳሙኤል ፊት አሳለፋቸው። ሳሙኤልም እሴይን። እግዚአብሔር እነዚህን አልመረጠም አለው።
- 11
ሳሙኤልም እሴይን። የቀረ ሌላ ልጅ አለህን? አለው። እርሱም። ታናሹ ገና ቀርቶአል፤ እነሆም፥ በጎችን ይጠብቃል አለ። ሳሙኤልም እሴይን። እርሱ እስኪመጣ ድረስ አንረፍቅምና ልከህ አስመጣው አለው።
- 12
ልኮም አስመጣው፤ እርሱም ቀይ፥ ዓይኑም የተዋበ፥ መልኩም ያማረ ነበረ። እግዚአብሔርም። ይህ ነውና ተነሥተህ ቅባው አለ።
- 13
ሳሙኤልም የዘይቱን ቀንድ ወስዶ በወንድሞቹ መካከል ቀባው። የእግዚአብሔርም መንፈስ ከዚያ ቀን ጀምሮ በዳዊት ላይ በኃይል መጣ። ሳሙኤልም ተነሥቶ ወደ አርማቴም ሄደ።
- 14
የእግዚአብሔርም መንፈስ ከሳኦል ራቀ፥ ክፉም መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ አሠቃየው።
- 15
የሳኦልም ባሪያዎች። እነሆ ክፉ መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያሠቃይሃል፤
- 16
በገና መልካም አድርጎ የሚመታ ሰው ይሹ ዘንድ ጌታችን በፊቱ የሚቆሙትን ባሪያዎቹን ይዘዝ፤ ከእግዚአብሔርም ዘንድ ክፉ መንፈስ በሆነብህ ጊዜ በእጁ ሲመታ አንተ ደኅና ትሆናለህ አሉት።
- 17
ሳኦልም ባሪያዎቹን። መልካም አድርጎ በገና መምታት የሚችል ሰው ፈልጋችሁ አምጡልኝ አላቸው።
- 18
ከብላቴኖቹም አንዱ መልሶ። እነሆ፥ መልካም አድርጎ በገና የሚመታ የቤተ ልሔማዊውን የእሴይን ልጅ አይቻለሁ፤ እርሱም ጽኑዕ ኃያል ነው፥ በነገርም ብልህ፥ መልኩም ያማረ ነው፥ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነው አለ።
- 19
ሳኦልም ወደ እሴይ መልክተኞች ልኮ። ከበጎች ጋር ያለውን ልጅህን ዳዊትን ላክልኝ አለ።
- 20
እሴይም እንጀራና የወይን ጠጅ አቁማዳ የተጫነ አህያ የፍየልም ጠቦት ወስዶ በልጁ በዳዋት እጅ ወደ ሳኦል ላከ።
- 21
ዳዊትም ወደ ሳኦል መጣ፥ በፊቱም ቆመ፤ እጅግም ወደደው፥ ለእርሱም ጋሻ ጃግሬው ሆነ።
- 22
ሳኦልም ወደ እሴይ። በዓይኔ ሞገስ አግኝቶአልና ዳዊት በፊቴ፥ እባክህ፥ ይቁም ብሎ ላከ።
- 23
እንዲህም ሆነ፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ ክፉ መንፈስ በሳኦል ላይ በሆነ ጊዜ ዳዊት በገና ይዞ በእጁ ይመታ ነበር፤ ሳኦልንም ደስ ያሰኘው ያሳርፈውም ነበር፥ ክፉ መንፈስም ከእርሱ ይርቅ ነበር።