1 Samuel 15
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
ሳሙኤልም ሳኦልን አለው። በሕዝቡ በእስራኤል ላይ ንጉሥ እንድትሆን እቀባህ ዘንድ እግዚአብሔር ላከኝ፥ አሁንም የእግዚአብሔርን ድምፅ ስማ።
- 2
የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እስራኤል ከግብጽ በወጣ ጊዜ አማሌቅ በመንገድ እየተቃወመ ያደረገበትን እበቀላለሁ።
- 3
አሁንም ሄደህ አማሌቅን ምታ፥ ያላቸውንም ሁሉ ፈጽመህ አጥፋ፥ አትማራቸውም፤ ወንዱንና ሴቱን ብላቴናውንና ሕፃኑን በሬውንና በጉን ግመሉንና አህያውን ግደል።
- 4
ሳኦልም ሕዝቡን ጠርቶ በጌልገላ ቈጠራቸው፤ ሁለት መቶ ሺህ እግረኞች፥ ከይሁዳም አሥር ሺህ ሰዎች ነበሩ።
- 5
ሳኦልም ወደ አማሌቅ ከተማ ወጣ፥ በሸለቆውም ውስጥ ተደበቀ።
- 6
ሳኦል ቄናውያንን። ተነሥታችሁ ሂዱ፤ ከግብጽ በወጡ ጊዜ ለእስራኤል ልጆች ቸርነት አድርጋችኋልና ከአማሌቅ ጋር እንዳላጠፋችሁ ከመካከላቸው ውረዱ አላቸው፤ ቄናውያንም ከአማሌቃውያን መካከል ሄዱ።
- 7
ሳኦልም አማሌቃውያንን ከኤውላጥ ጀምሮ በግብጽ ፊት እስካለችው እስከ ሱር ድረስ መታቸው።
- 8
የአማሌቅንም ንጉሥ አጋግን በሕይወቱ ማረከው፥ ሕዝቡንም ሁሉ በሰይፍ ስለት ፈጽሞ አጠፋቸው።
- 9
ነገር ግን ሳኦልና ሕዝቡ ለአጋግ፥ ለተመረጡትም በጎችና በሬዎች ለሰቡትም ጥጆችና ጠቦቶች፥ ለመልካሞቹም ሁሉ ራሩላቸው፥ ፈጽሞ ሊያጠፉአቸውም አልወደዱም፤ ነገር ግን ምናምንቴንና የተናቀውን ሁሉ ፈጽመው አጠፉት።
- 10
- 11
ሳሙኤልም በነጋው ሳኦልን ለመገናኘት ማለደ። ሳኦልም ወደ ቀርሜሎስ መጣ፤ እነሆም፥ የመታሰቢያ ዓምድ ባቆመ ጊዜ ዞሮ አለፈ፥ ወደ ጌልገላም ወረደ የሚል ወሬ ለሳሙኤል ደረሰለት።
- 12
ሳሙኤልም ወደ ሳኦል መጣ፤ ሳኦልም። አንተ ለእግዚአብሔር የተባረክህ ሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ፈጽሜአለሁ አለው።
- 13
ሳሙኤልም። ይህ በጆሮዬ የምሰማው የበጎች ጩኸትና የበሬዎች ግሣት ምንድር ነው? አለ።
- 14
ሳኦልም። ሕዝቡ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ይሠዉአቸው ዘንድ መልካሞቹን በጎችና በሬዎች አድነዋቸዋልና ከአማሌቃውያን አምጥተዋቸዋል፤ የቀሩትንም ፈጽመን አጠፋን አለው።
- 15
ሳሙኤልም ሳኦልን። ቆይ፥ እግዚአብሔር ዛሬ ሌሊት የነገረኝን ልንገርህ አለው፤ እርሱም። ተናገር አለው።
- 16
ሳሙኤልም አለ። በዓይንህ ምንም ታናሽ ብትሆን ለእስራኤል ነገዶች አለቃ አልሆንህምን? እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆን ዘንድ ቀባህ።
- 17
እግዚአብሔርም። ሄደህ ኃጢአተኞቹን አማሌቃውያንን ፈጽመህ አጥፋቸው፥ እስኪጠፉም ድረስ ውጋቸው ብሎ በመንገድ ላከህ።
- 18
ለምርኮ ሳስተህ ለምን የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማህም? ለምንስ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረግህ?
- 19
ሳኦልም ሳሙኤልን። የእግዚአብሔርን ቃል ሰምቻለሁ፥ እግዚአብሔርም በላከኝ መንገድ ሄጃለሁ፤ የአማሌቅን ንጉሥ አጋግን አምጥቻለሁ፥ አማሌቃውያንንም ፈጽሜ አጥፍቻለሁ።
- 20
ሕዝቡ ግን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር በጌልገላ ይሠዉ ዘንድ ከእርሙ የተመረጡትን በጎችንና በሬዎችን ከምርኮው ወሰዱ አለው።
- 21
ሳሙኤልም። በውኑ የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት ደስ እንደሚለው እግዚአብሔር በሚቃጠልና በሚታረድ መሥዋዕት ደስ ይለዋልን? እነሆ፥ መታዘዝ ከመሥዋዕት፥ ማዳመጥም የአውራ በግ ስብ ከማቅረብ ይበልጣል።
- 22
ዓመፀኝነት እንደ ምዋርተኛ ኃጢአት፥ እልከኝነትም ጣዖትንና ተራፊምን እንደ ማምለክ ነው፤ የእግዚአብሔርን ቃል ንቀሃልና እግዚአብሔር ንጉሥ እንዳትሆን ናቀህ አለ።
- 23
ሳኦልም ሳሙኤልን። ሕዝቡን ስለ ፈራሁ፥ ቃላቸውንም ስለ ሰማሁ የእግዚአብሔርን ትእዛዝና የአንተን ቃል በመተላለፍ በድያለሁ።
- 24
አሁንም፥ እባክህ፥ ኃጢአቴን ይቅር በለኝ፥ ለእግዚአብሔርም እሰግድ ዘንድ ከእኔ ጋር ተመለስ አለው።
- 25
ሳሙኤልም ሳኦልን። የእግዚአብሔርን ቃል ንቀሃልና፥ እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ንጉሥ እንዳትሆን ንቆሃልና ከአንተ ጋር አልመለስም አለው።
- 26
ሳሙኤልም ሊሄድ ዘወር ባለ ጊዜ ሳኦል የልብሱን ጫፍ ያዘ፥ ተቀደደም።
- 27
ሳሙኤልም። እግዚአብሔር የእስራኤልን መንግሥት ዛሬ ከአንተ ቀደዳት፥ ከአንተም ለሚሻል ለጎረቤትህ አሳልፎ ሰጣት፤
- 28
የእስራኤል ኃይል እንደ ሰው የሚጸጸት አይደለምና አይዋሽም አይጸጸትምም አለው።
- 29
እርሱም። በድያለሁ፤ አሁን ግን በሕዝቤ ሽማግሌዎች ፊትና በእስራኤል ፊት፥ እባክህ፥ አክብረኝ፤ ለአምላክህም ለእግዚአብሔር እሰግድ ዘንድ ከእኔ ጋር ተመለስ አለው።
- 30
ሳሙኤልም ከሳኦል በኋላ ተመለሰ፤ ሳኦልም ለእግዚአብሔር ሰገደ።
- 31
ሳሙኤልም። የአማሌቅን ንጉሥ አጋግን አምጡልኝ አለ። አጋግም እየተንቀጠቀጠ ወደ እርሱ መጣ። አጋግም። በውኑ ሞት እንደዚህ መራራ ነውን? አለ።
- 32
ሳሙኤልም። ሰይፍህ ሴቶችን ልጆች አልባ እንዳደረገቻቸው እንዲሁ እናትህ በሴቶች መካከል ልጅ አልባ ትሆናለች አለ፤ ሳሙኤልም አጋግን በእግዚአብሔር ፊት በጌልገላ ቈራረጠው።
- 33
ሳሙኤልም ወደ አርማቴም ሄደ፤
- 34
ሳኦልም ወደ ቤቱ ወደ ጊብዓ ወጣ። ሳሙኤልም እስከ ሞተበት ቀን ድረስ ሳኦልን ለማየት ዳግመኛ አልሄደም፥ ሳሙኤልም ለሳኦል አለቀሰ፤ እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ሳኦልን ስላነገሠ ተጸጸተ።