Psalms 73
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
ልባቸው ለቀና ለእስራኤል እግዚአብሔር እንዴት ቸር ነው።
- 2
እኔ ግን እግሮቼ ሊሰናከሉ፥ አረማመዴም ሊወድቅ ትንሽ ቀረ።
- 3
የኃጢአተኞችን ሰላም አይቼ በዓመፀኞች ቀንቼ ነበርና።
- 4
ለሞታቸው መጣጣር የለውምና፤ ኃይላቸውም ጠንካራ ነውና።
- 5
እንደ ሰው በድካም አልሆኑም፥ ከሰው ጋርም አልተገረፉም።
- 6
ስለዚህ ትዕቢት ያዛቸው፤ ኃጢአትንና በደልን ተጐናጸፉአት።
- 7
ዓይናቸው ስብ ስለ ሆነ ወጣ፤ ልባቸውም ከምኞታቸው ይልቅ አገኘ።
- 8
አስበው ክፉ ነገርን ተናገሩ። ከፍ ከፍ ብለውም በዓመፃ ተናገሩ።
- 9
አፋቸውን በሰማይ አኖሩ፥ አንደበታቸውም በምድር ውስጥ ተመላለሰ።
- 10
ስለዚህ ሕዝቤ ወደዚህ ይመለሳሉ፤ ፍጹም ጊዜም በላያቸው ይገኛል፤
- 11
እግዚአብሔር እንዴት ያውቃል? በልዑልስ ዘንድ በውኑ እውቀት አለ? ይላሉ።
- 12
እነሆ፥ እነዚህ ኃጢአተኞች ይደሰታሉ፥ ሁልጊዜም ባለጠግነታቸውን ያበዛሉ።
- 13
እንዲህም አልሁ። በውኑ ልቤን በከንቱ አጸደቅሁ፥ እጆቼንም በንጽሕና በከንቱ አጠብሁ።
- 14
ሁልጊዜም የተገረፍሁ ሆንሁ፥ መሰደቤም በማለዳ ነው።
- 15
እንደዚህ ብዬ ብናገር ኖሮ፥ እነሆ፥ የልጆችህን ትውልድ በበደልሁ ነበር።
- 16
አውቅም ዘንድ አሰብሁ፥ ይህ ግን በፊቴ ችግር ነበረ።
- 17
ወደ እግዚአብሔር መቅደስ እስክገባ ድረስ፥ ፍጻሜአቸውንም እስካስተውል ድረስ።
- 18
በድጥ ስፍራ አስቀመጥኻቸው፥ ወደ ጥፋትም ጣልኻቸው።
- 19
እንዴት ለጥፋት ሆኑ! በድንገት አለቁ ስለ ኃጢአታቸውም ጠፉ።
- 20
ከሕልም እንደሚነቃ፥ አቤቱ፥ ስትነቃ ምልክታቸውን ታስነውራለህ።
- 21
ልቤ ነድዶአልና፥ ኵላሊቴም ቀልጦአልና፤
- 22
እኔ የተናቅሁ ነኝ አላውቅሁምም፥ በአንተ ዘንድም እንደ እንስሳ ሆንሁ።
- 23
እኔ ግን ዘወትር ከአንተ ጋር ነኝ፥ ቀኝ እጄንም ያዝኸኝ።
- 24
በአንተ ምክር መራኸኝ፤ ከክብር ጋር ተቀበልኸኝ።
- 25
በሰማይ ያለኝ ምንድር ነው? በምድርስ ውስጥ ከአንተ ዘንድ ምን እሻለሁ?
- 26
የልቤ አምላክ ሆይ፥ ልቤና ሥጋዬ አለቀ፤ እግዚአብሔር ግን ለዘላለም እድል ፈንታዬ ነው።
- 27
እነሆ፥ ከአንተ የሚርቁ ይጠፋሉና ከአንተ ርቀው የሚያመነዝሩትንም ሁሉ አጠፋኻቸው።
- 28
ለእኔ ግን ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ይሻለኛል፤ መታመኛዬም እግዚአብሔር ነው በጽዮን ልጅ በሮች ምስጋናህን ሁሉ እናገር ዘንድ።