Psalms 69
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
አቤቱ፥ ውኃ እስከ ነፍሴ ደርሶብኛልና አድነኝ።
- 2
በጥልቅ ረግረግ ጠለቅሁ መቋሚያም የለኝም። ወደ ጥልቅ ባሕር ገባሁ ማዕበልም አሰጠመኝ።
- 3
በጩኸት ደከምሁ ጕሮሮዬም ሰለለ፤ አምላኬን ስጠብቅ ዓይኖቼ ፈዘዙ።
- 4
በከንቱ የሚጠሉኝ ከራሴ ጠጕር በዙ፤ በዓመፅ ያሚያሳድዱኝ ጠላቶቼ በረቱ፤ በዚያን ጊዜ ያልቀማሁትን መለስሁ።
- 5
አቤቱ፥ አንተ ስንፍናዬን ታውቃለህ፥ ኃጢአቴም ከአንተ አልተሰወረም።
- 6
አቤቱ የሠራዊት አምላክ፥ ተስፋ የሚያደርጉህ በእኔ አይፈሩ፤ የእስራኤል አምላክ ሆይ፥ የሚሹህ በእኔ አይነወሩ።
- 7
ስለ አንተ ስድብን ታግሻለሁና፥ እፍረትም ፊቴን ሸፍናለችና።
- 8
ለወንድሞቼ እንደ ሌላ፥ ለእናቴ ልጆችም እንደ እንግዳ ሆንሁባቸው፥
- 9
የቤትህ ቅንዓት በልታኛለችና፥ የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ወድቆአልና።
- 10
ነፍሴን በጾም አስመረርሁአት፥ ለስድብም ሆነብኝ።
- 11
ማቅ ለበስሁ ምሳሌም ሆንሁላቸው።
- 12
በደጅ የሚቀመጡ በእኔ ይጫወታሉ፤ ወይን የሚጠጡ እኔን ይዘፍናሉ።
- 13
አቤቱ፥ በመልካሙ ጊዜ ጸሎቴ ወደ አንተ ነው፤ አቤቱ፥ በምሕረትህ ብዛት በማዳንህም እውነት አድምጠኝ።
- 14
እንዳይውጠኝ ከረግረግ አውጣኝ፤ ከሚጠሉኝና ከጥልቅ ውኃ አስጥለኝ።
- 15
የውኃው ማዕበል አያስጥመኝ፥ ጥልቁም አይዋጠኝ፥ ጕድጓድም አፉን በእኔ ላይ አይዝጋ።
- 16
አቤቱ፥ ምሕረትህ መልካም ናትና ስማኝ። እንደ ርኅራኄህም ብዛት ወደ እኔ ተመልከት፤
- 17
ከባሪያህም ፊትህን አትሰውር፤ ተጨንቄአለሁና ፈጥነህ አድምጠኝ።
- 18
ነፍሴን ተመልክተህ ተቤዣት፤ ስለ ጠላቶቼም አድነኝ።
- 19
አንተ ስድቤን እፍረቴንም ነውሬንም ታውቃለህ፤ የሚያስጨንቁኝ ሁሉ በፊትህ ናቸው።
- 20
ነፍሴ ስድብንና ኃሣርን ታገሠች፤ አስተዛዛኝም ተመኘሁ አላገኘሁም። የሚያጽናናኝም አጣሁ።
- 21
ለመብሌ ሐሞት ሰጡኝ፥ ለጥማቴም ሆምጣጤ አጠጡኝ።
- 22
ማዕዳቸው በፊታቸው ለወጥመድ ለፍዳ ለዕንቅፋት ትሁንባቸው፤
- 23
ዓይኖቻቸው እንዳያዩ ይጨልሙ፥ ጀርባቸውም ዘወትር ይጕበጥ።
- 24
መዓትህን በላያቸው አፍስስ፥ የቍጣህ መቅሠፍትም ያግኛቸው።
- 25
ማደሪያቸው በረሃ ትሁን፥ በድንኳኖቻቸውም የሚቀመጥ አይገኝ፤
- 26
አንተ የቀሠፍኸውን እነርሱ አሳድደዋልና፥ በቍስሌም ላይ ጥዝጣዜ ጨመሩብኝ።
- 27
በኃጢአታቸው ላይ ኃጢአትን ጨምርባቸው፥ በጽድቅህም አይግቡ።
- 28
ከሕያዋን መጽሐፍ ይደምሰሱ፥ ከጻድቃንም ጋር አይጻፉ።
- 29
እኔ ችግረኛና ቍስለኛ ነኝ፤ አቤቱ፥ የፊትህ መድኃኒት ይቀበለኝ።
- 30
የእግዚአብሔርን ስም በዝማሬ አመሰግናለሁ፥ በምስጋናም ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ።
- 31
ቀንድና ጥፍር ካበቀለ ከእምቦሳ ይልቅ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋል።
- 32
ችግረኞች ያያሉ ደስ ይላቸዋል፤ እግዚአብሔርን ፈልጉ ሕያዋንም ሁኑ።
- 33
እግዚአብሔር ችግረኞችን ሰምቶአልና፥ እስረኞቹንም አልናቀምና።
- 34
ሰማይና ምድር ባሕርም በእርስዋም የሚንቀሳቀስ ሁሉ ያመሰግኑታል።
- 35
እግዚአብሔር ጽዮንን ያድናታልና፥ የይሁዳንም ከተሞች ይሠራልና፤ በዚያም ይቀመጣሉ ይወርሱአትማል።
- 36
የባሪያዎቹ ዘር ይኖሩባታል። ስሙንም የሚወድዱ በዚያ ይቀመጣሉ።