Psalms 55
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
አቤቱ፥ ጸሎቴን አድምጥ፥ ልመናዬንም ቸል አትበል።
- 2
ተመልከተኝ ስማኝም። በኀዘኔ ተቅበዘበዝሁ ተናወጥሁም፤
- 3
ከጠላት ድምፅ ከዓመፀኛም ግፍ የተነሣ፤ ዓመፃን በላዬ ጥለውብኛልና፥ በቁጣም ጠልተውኛልና።
- 4
ልቤ በላዬ ተናወጠብኝ፥ የሞት ድንጋጤም ወደቀብኝ።
- 5
ፍርሃትና እንቅጥቅጥ መጡብኝ፥ ጨለማም ሸፈነኝ።
- 6
በርሬ ዐርፍ ዘንድ እንደ ርግብ ክንፍን ማን በሰጠኝ!
- 7
እነሆ፥ ኰብልዬ በራቅሁ በምድረ በዳም በተቀመጥሁ፤
- 8
ከዐውሎና ከብርቱ ንፋስ ሸሽቼ በፈጠንሁ አልሁ።
- 9
አቤቱ፥ ግፍንና ጠብን በከተማ ውስጥ አይቼአለሁና አስጥማቸው እንደበታቸውንም ቍረጥ።
- 10
በቀንና በሌሊት በቅጥርዋ ይከብቡአታል፤ ዓመፃና ድካም ኃጢአትም በመካከልዋ ነው፤
- 11
ተንኰልና ሽንገላ ከአደባባይዋ አይርቁም።
- 12
ጠላትስ ቢሰድበኝ፥ በታገሥሁ ነበር፤ የሚጠላኝም ራሱን በላዬ ከፍ ከፍ ቢያደርግ፥ ከእርሱ በተሸሸግሁ ነበር።
- 13
አንተ ግን፥ እኩያዬ ሰው፥ ባልንጀራዬና የልቤ ወዳጅ፤
- 14
መብልን ከእኔ ጋር በአንድነት ያጣፈጥህ፤ በአንድ ልብ በእግዚአብሔር ቤት ተራመድን።
- 15
ሞት ይምጣባቸው፤ በሕይወት ሳሉ ወደ ሲኦል ይውረዱ፤ ክፋት በማደሪያቸውና በመካከላቸው ነውና።
- 16
እኔ ግን ወደ እግዚአብሔር ጮኽሁ፥ እግዚአብሔርም ሰማኝ።
- 17
በማታና በጥዋት በቀትርም እናገራለሁ እጮኽማለሁ፥ ቃሌንም ይሰማኛል።
- 18
በእኔ ላይ ብዙ ነበሩና ከሚቃረቡኝ ነፍሴን በሰላም አድናት።
- 19
ቤዛ የላቸውምና፥ እግዚአብሔርንም አልፈሩትምና ከጥንት ጀምሮ የነበረ እግዚአብሔር ሰምቶ ያጐሰቍላቸዋል።
- 20
ከእርሱ ጋር ሰላም በነበሩት ላይ እጁን ዘረጋ፤ ኪዳኑንም አረከሱ።
- 21
አፉ ከቅቤ ይልቅ ለዘበ፥ በልቡ ግን ሰልፍ ነበረ፤ ቃሎቹም ከዘይት ይልቅ ለሰለሱ፥ እነርሱ ግን እንደ ተመዘዘ ሰይፍ ናቸው።
- 22
ትካዜህን በእግዚአብሔር ላይ ጣል፥ እርሱም ይደግፍሃል፤ ለጻድቁም ለዘላለም ሁከትን አይሰጠውም።
- 23
አንተ ግን፥ አቤቱ፥ ወደ ሞት ጕድጓድ ታወርዳቸዋለህ፤ የደም ሰዎችና ሸንጋዮች ዘመናቸው ግማሽ አይሞላም፤ እኔ ግን፥ አቤቱ፥ እታመንሃለሁ።