Psalms 18
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
አቤቱ ጕልበቴ ሆይ፥ እወድድሃለሁ።
- 2
እግዚአብሔር ዓለቴ፥ አምባዬ፥ መድኃኒቴ፥ አምላኬ፥ በእርሱም የምተማመንበት ረዳቴ፥ መታመኛዬና የደኅንነቴ ቀንድ መጠጊያዬም ነው።
- 3
ምስጋና የሚገባውን እግዚአብሔርን እጠራለሁ፥ ከጠላቶቼም እድናለሁ።
- 4
የሞት ጣር ያዘኝ፥ የዓመፅ ፈሳሽም አስፈራኝ፤
- 5
የሲኦል ጣር ከበበኝ፤ የሞት ወጥመድም ደረሰብኝ።
- 6
በጨነቀኝ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፥ ወደ አምላኬም ጮኽሁ፤ ከመቅደሱም ቃሌን ሰማኝ፥ ጩኸቴም በፊቱ ወደ ጆሮው ገባ።
- 7
ምድርም ተንቀጠቀጠች ተናወጠችም፥ የተራሮችም መሠረቶች ተነቃነቁ፥ እግዚአብሔርም ተቈጥቶአልና ተንቀጠቀጡ።
- 8
ከቍጣው ጢስ ወጣ፥ ከፊቱም የሚበላ እሳት ነደደ፤ ፍምም ከእርሱ በራ።
- 9
ሰማዮችን ዝቅ ዝቅ አደረገ ወረደም፥ ጨለማ ከእግሩ በታች ነበረ።
- 10
በኪሩቤልም ላይ ተቀምጦ በረረ፥ በነፋስም ክንፍ በረረ።
- 11
መሰወሪያውን ጨለማ አደረገ፤ በዙሪያውም ድንኳኑ፤ በደመናት ውስጥ የጨለማ ውኃ ነበረ።
- 12
በፊቱ ካለው ብርሃን የተነሣ ደመናትና በረዶ የእሳት ፍምም አለፉ።
- 13
እግዚአብሔርም ከሰማያት አንጐደጐደ፥ ልዑልም ቃሉን ሰጠ።
- 14
ፍላጻውን ላከ በተናቸውም፤ መብረቆችን አበዛ አወካቸውም።
- 15
አቤቱ፥ ከዘለፋህ ከመዓትህም መንፈስ እስትንፋስ የተነሣ፥ የውኆች ምንጮች ታዩ፥ የዓለም መሠረቶችም ተገለጡ።
- 16
ከላይ ሰደደ ወሰደኝም፥ ከብዙ ውኆችም አወጣኝ።
- 17
ከብርቱዎች ጠላቶቼ ከሚጠሉኝም አዳነኝ፥ በርትተውብኝ ነበርና።
- 18
በመከራዬ ቀን ደረሱብኝ፤ እግዚአብሔር ግን ደገፋዬ ሆነ።
- 19
ወደ ሰፊ ስፍራም አወጣኝ፤ ወድዶኛልና አዳነኝ።
- 20
እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ ይከፍለኛል፤ እንደ እጄ ንጽሕና ይመልስልኛል።
- 21
የእግዚአብሔርን መንገድ ጠብቄአለሁና፥ በአምላኬም አላመፅሁም።
- 22
ፍርዱ ሁሉ በፊቴ ነበረና፥ ሥርዓቱንም ከፊቴ አላራቅሁም።
- 23
በእርሱ ዘንድ ቅን ነበርሁ፥ ከኃጢአቴም ተጠበቅሁ።
- 24
እግዚአብሔርም እንደ ጽድቄ እንደ እጄም ንጽሕና በዓይኖቹ ፊት መለሰልኝ።
- 25
ከቸር ሰው ጋር ቸር ሆነህ ትገኛለህ፤ ከቅን ሰው ጋር ቅን ሆነህ ትገኛለህ፤
- 26
ከንጹሕ ጋር ንጹሕ ሆነህ ትገኛለህ፤ ከጠማማም ጋር ጠማማ ሆነህ ትገኛለህ።
- 27
አንተ የተጠቃውን ሕዝብ ታድናለህና፥ የትዕቢተኞችን ዓይን ግን ታዋርዳለህ።
- 28
አንተ መብራቴን ታበራለህና፤ እግዚአብሔር አምላኬ ጨለማዬን ያበራል።
- 29
በአንተ ከጥፋት እድናለሁና በአምላኬም ቅጥሩን እዘልላለሁ።
- 30
የአምላኬ መንገድ ፍጹም ነው፥ የእግዚአብሔር ቃል የነጠረ ነው፥ በእርሱ ለሚታመኑት ሁሉ ጋሻ ነው።
- 31
ከእግዚአብሔር በቀር አምላክ ማን ነው? ከአምላካችን በቀር አምላክ ማን ነው?
- 32
ኃይልን የሚያስታጥቀኝ መንገዴንም የሚያቃና፥
- 33
እግሮቼን እንደ ብሖር እግሮች የሚያረታ በኮረብቶችም የሚያቆመኝ እግዚአብሔር ነው።
- 34
እጆቼን ሰልፍ ያስተምራል፥ በክንዴም የናስ ቀስት እገትራለሁ።
- 35
ለደኅንነቴም መታመኛን ሰጠኸኝ፥ ቀኝህም ትረዳኛለች፥ ትምህርትህም ለዘላለም ታጠናኛለች፥ ተግሣጽህም ታስተምረኛለች።
- 36
አረማመዴን በበታቼ አሰፋህ፥ እግሮቼም አልተንሸራተቱም።
- 37
ጠላቶቼን አሳድዳቸዋለሁ እይዛቸዋለሁም፥ እስካጠፋቸውም ድረስ አልመለስም።
- 38
አስጨንቃቸዋለሁ መቆምም አይችሉም፥ ከእግሬም በታች ይወድቃሉ።
- 39
ለሰልፍም ኃይልን ታስታጥቀኛለህ፤ በበላዬ የቆሙትን ሁሉ በበታቼ ታስገዛቸዋለህ።
- 40
የጠላቶቼን ጀርባ ሰጠኸኝ፥ የሚጠሉኝንም አጠፋሃቸው።
- 41
ጮኹ የሚረዳቸውም አልነበረም፤ ወደ እግዚአብሔርም ጮኹ አልሰማቸውም።
- 42
እንደ ትቢያ በነፋስ ፊት እፈጫቸዋለሁ፥ እንደ አደባባይም ጭቃ እረግጣቸዋለሁ።
- 43
ከሕዝብ ክርክር ታድነኛለህ፥ የአሕዛብም ራስ አድርገህ ትሾመኛለህ፥ የማላውቀው ሕዝብም ይገዛልኛል።
- 44
በጆሮ ሰምተው ተገዙልኝ፤ የባዕድ ልጆች ደለሉኝ።
- 45
የባዕድ ልጆች አረጁ፥ በመንገዳቸውም ተሰናከሉ።
- 46
እግዚአብሔር ሕያው ነው፥ አምላኬም ቡሩክ ነው፥ የመድኃኒቴም አምላክ ከፍ ከፍ ይበል።
- 47
በቀሌን የሚመልስልኝ አምላክ አሕዛብን በበታቼ ያስገዛልኛል።
- 48
ከጠላቶቼ የሚታደገኝ እርሱ ነው፤ በእኔም ላይ ከቆሙ ከፍ ከፍ ታደርገኛለህ፥ ከግፈኛ ሰው ታድነኛለህ።
- 49
አቤቱ፥ ስለዚህ በአሕዛብ ዘንድ አመሰግንሃለሁ፥ ለስምህም እዘምራለሁ።
- 50
የንጉሡን መድኃኒት ታላቅ ያደርጋል፥ ቸርነቱንም ለቀባው ለዳዊትና ለዘሩ ለዘላለም ይሰጣል።