Psalms 118
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
እግዚአብሔርን አመስግኑ፥ ቸር ነውና፤ ምሕረቱ ለዘላለም ናትና።
- 2
ቸር እንደ ሆነ፥ ምሕረቱ ለዘላለም እንደ ሆነች የእስራኤል ቤት አሁን ይንገሩ።
- 3
ቸር እንደ ሆነ፥ ምሕረቱ ለዘላለም እንደ ሆነች የአሮን ቤት አሁን ይንገሩ።
- 4
ቸር እንደ ሆነ፥ ምሕረቱ ለዘላለም እንደ ሆነች እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሁሉ አሁን ይንገሩ።
- 5
በተጨነቅሁ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፤ ሰማኝ አሰፋልኝም።
- 6
እግዚአብሔር ረዳቴ ነው፥ አልፈራም ሰው ምን ያደርገኛል?
- 7
እግዚአብሔር ረዳቴ ነው፥ እኔም በጠላቶቼ ላይ አያለሁ።
- 8
በሰው ከመታመን ይልቅ በእግዚአብሔር መታመን ይሻላል።
- 9
በገዦች ተስፋ ከማድረግ ይልቅ በእግዚአብሔር ተስፋ ማድረግ ይሻላል።
- 10
አሕዛብ ሁሉ ከበቡኝ፥ በእግዚአብሔርም ስም አሸነፍኋቸው፤
- 11
መክበቡንስ ከበቡኝ፥ በእግዚአብሔርም ስም አሸነፍኋቸው፤
- 12
ንብ ማርን እንዲከብብ ከበቡኝ፥ እሳትም በእሾህ ውስጥ እንዲነድድ ነደዱ፥ በእግዚአብሔርም ስም አሸነፍኋቸው።
- 13
ገፋኸኝ፥ ለመውደቅም ተንገዳገድሁ፤ እግዚአብሔር ግን አገዘኝ።
- 14
ኃይሌም ዝማሬዬም እግዚአብሔር ነው፥ እርሱም መድኃኒት ሆነልኝ።
- 15
የእልልታና የመድኃኒት ድምፅ በጻድቃን ድንኳን ነው፤ የእግዚአብሔር ቀኝ ኃይልን አደረገች።
- 16
የእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ አደረገችኝ፤ የእግዚአብሔር ቀኝ ኃይልን አደረገች።
- 17
አልሞትም በሕይወት እኖራለሁ እንጂ፥ የእግዚአብሔርንም ሥራ እናገራለሁ።
- 18
መገሠጽስ እግዚአብሔር ገሠጸኝ፤ ለሞት ግን አልሰጠኝም።
- 19
የጽድቅን ደጆች ክፈቱልኝ፤ ወደ እነርሱ ገብቼ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ።
- 20
ይህች የእግዚአብሔር ደጅ ናት፤ ወደ እርስዋ ጻድቃን ይገባሉ።
- 21
ሰምተኸኛልና፥ መድኃኒትም ሆነኸኛልና አመሰግንሃለሁ።
- 22
ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፥ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ፥
- 23
ይህች ከእግዚአብሔር ዘንድ ሆነች፥ ለዓይናችንም ድንቅ ናት።
- 24
እግዚአብሔር የሠራት ቀን ይህች ናት፤ ሐሤትን እናድርግ፥ በእርስዋም ደስ ይበለን።
- 25
አቤቱ፥ እባክህ፥ አሁን አድን፤ አቤቱ፥ እባክህ፥ አሁን አቅና።
- 26
በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው፤ ከእግዚአብሔር ቤት መረቅናችሁ።
- 27
እግዚአብሔር አምላክ ነው፥ ለእኛም በራልን፤ እስከ መሠዊያው ቀንዶች ድረስ የበዓሉን መሥዋዕት በገመድ እሰሩት።
- 28
አንተ አምላኬ ነህ አመሰግንህማለሁ። አንተ አምላኬ ነህ፥ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ፤ ሰምተኸኛልና፥ መድኃኒትም ሆነኸኛልና አመሰግንሃለሁ።
- 29
እግዚአብሔርን አመስግኑ፥ ቸር ነውና፤ ምሕረቱ ለዘላለም ናትና።