Proverbs 8
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
በውኑ ጥበብ አትጮኽምን? ማስተዋልስ ድምፅዋን አትሰጥምን?
- 2
በኮረብታ ላይ በመንገድ አጠገብ በጎዳና መካከል ትቆማለች።
- 3
በበሩ አጠገብ በከተማይቱም መግቢያ፥ በደጁ መግቢያ ትጮኻለች።
- 4
እናንተ ሰዎች፥ እናንተን እጠራለሁ፥ ድምፄም ወደ ሰዎች ልጆች ነው።
- 5
እናንተ አላዋቂዎች፥ ብልሃትን አስተውሉ፤ እናንተም ሰነፎች ጥበብን በልባችሁ ያዙ።
- 6
የከበረች ነገርን እናገራለሁና ስሙ፤ ከንፈሮቼም ቅን ነገርን ለመናገር ይከፈታሉ።
- 7
አፌ እውነትን ይናገራልና፥ ከንፈሮቼም ክፋትን ይጸየፋሉ።
- 8
የአፌ ቃላት ሁሉ ጽድቅ ናቸው፤ ጠማማ ዘወርዋራም አይደሉም።
- 9
እነርሱ በሚያስተውሉ ዘንድ የቀኑ ናቸው፥ እውቀትንም ካገኙአት ሰዎች ጋር የተስማሙ ናቸው።
- 10
ተግሣጼን እንጂ ብርን አትቀበሉ፥ ከምዝምዝ ወርቅም ይልቅ እውቀትን ተቀበሉ።
- 11
ጥበብ ከቀይ ዕንቍ ትበልጣለችና የከበረ ነገር ሁሉ አይተካከላትም።
- 12
እኔ ጥበብ በብልሃት ተቀምጫለሁ፥ እውቀትንም ጥንቃቄንም አግኝቻለሁ።
- 13
እግዚአብሔርን መፍራት ክፋትን ይጠላል፤ ትዕቢትንና እብሪትን ክፉንም መንገድ ጠማማውንም አፍ እጠላለሁ።
- 14
ምክርና መልካም ጥበብ የእኔ ነው፤ ማስተዋል እኔ ነኝ፥ ብርታትም አለኝ።
- 15
ነገሥታት በእኔ ይነግሣሉ፥ ሹማምቶችም የቀናውን ነገር ይደነግጋሉ።
- 16
አለቆች በእኔ ያዝዛሉ፥ ክቡራንና የምድር ፈራጆችም ሁሉ።
- 17
እኔ የሚወድዱኝን እወድዳለሁ፥ ተግተው የሚሹኝም ያገኙኛል።
- 18
ብልጥግናና ክብር በእኔ ዘንድ ነው፥ ብዙ ሀብትና ጽድቅም።
- 19
ፍሬዬም ከምዝምዝ ወርቅ ይሻላል፥ ቡቃያዬም ከተመረጠች ብር።
- 20
እኔ በጽድቅ መንገድ እሄዳለሁ፥ በፍርድም ጎዳና መካከል፥
- 21
ለሚወድዱኝ ርስት አወርሳቸው ዘንድ ቤተ መዛግብታቸውንም እሞላ ዘንድ።
- 22
እግዚአብሔር የመንገዱ መጀመሪያ አደረገኝ፥ በቀድሞ ሥራው መጀመሪያ።
- 23
ከጥንቱ ከዘላለም ጀምሮ ተሾምሁ፤ ምድር ከመፈጠርዋ አስቀድሞ።
- 24
ቀላያት ገና ሳይኖሩ እኔ ተወለድሁ፥ የውኃ ምንጮች ገና ሳይፈልቁ።
- 25
ተራሮች ገና ሳይመሠረቱ፥ ከኮረብቶች በፊት እኔ ተወለድሁ፥
- 26
ምድሪቱንና ሜዳውን ገና ሳይፈጥር፤ የመጀመሪያውን የዓለም አፈር።
- 27
ሰማዮችን በዘረጋ ጊዜ አብሬ ነበርሁ፥ በቀላያት ፊት ክበብን በደነገገ ጊዜ፥
- 28
ደመናትን በላይ ባዘጋጀ ጊዜ፥ የቀላይን ምንጮች ባጸና ጊዜ፥
- 29
ለባሕርም ዳርቻን በወሰነ ጊዜ ውኃ ከትእዛዙ እንዳያልፍ፥ የምድርን መሠረት በመሠረተ ጊዜ፥
- 30
የዚያን ጊዜ እኔ በእርሱ ዘንድ ዋና ሠራተኛ ነበርሁ፤ ዕለት ዕለት ደስ አሰኘው ነበርሁ፥ በፊቱም ሁልጊዜ ደስ ይለኝ ነበርሁ፥
- 31
ደስታዬም በምድሩ ተድላዬም በሰው ልጆች ነበረ።
- 32
አሁንም ልጆቼ ሆይ፥ ስሙኝ፤ መንገዴንም የሚጠብቁ ምስጉኖች ናቸው።
- 33
ትምህርቴን ስሙ፥ ጠቢባንም ሁኑ፥ ቸል አትበሉትም።
- 34
የሚሰማኝ ሰው ምስጉን ነው ዕለት ዕለት በቤቴ መግቢያ የሚተጋ፥ የደጄንም መድረክ የሚጠብቅ።
- 35
እኔን ያገኘ ሕይወትን ያገኛልና። ከእግዚአብሔርም ሞገስን ያገኛልና።
- 36
እኔን ያጣ ግን ራሱን ይጐዳል፤ የሚጠሉኝ ሁሉ ሞትን ይወድዳሉ።