Proverbs 28
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
ኀጥእ ማንም ሳያሳድደው ይሸሻል፤ ጻድቅ ግን እንደ አንበሳ ያለ ፍርሃት ይኖራል።
- 2
ስለ አገሪቱ ዓመፀኝነት አለቆችዋ ብዙ ሆኑ፤ በአስተዋይና በአዋቂ ሰው ግን ዘመንዋ ይረዝማል።
- 3
ድሆችን የሚያስጨንቅ ምስኪን ሰው እህልን እንደሚያጠፋ እንደ ዶፍ ዝናብ ነው።
- 4
ሕግን የሚተዉ ሰዎች ኀጥኣንን ያመሰግናሉ፤ ሕግ ጠባቂዎች ግን ይጠሉአቸዋል።
- 5
ክፉዎች ሰዎች ፍርድን አያስተውሉም፤ እግዚአብሔርን የሚሹ ግን ሁሉን ያስተውላሉ።
- 6
በጠማማ መንገድ ከሚሄድ ባለጠጋ ያለ ነውር የሚሄድ ድሀ ይሻላል።
- 7
ሕግን የሚጠብቅ አስተዋይ ልጅ ነው፤ ምናምንቴዎችን የሚከተል ግን አባቱን ያሳፍራል።
- 8
በአራጣ ብዛትና በቅሚያ ሀብቱን የሚያበዛ ለድሀ ለሚራራ ያከማችለታል።
- 9
ሕግን ከመስማት ጆሮውን የሚመልስ ጸሎቱ አስጸያፊ ናት።
- 10
ቅኖችን በክፉ መንገድ የሚያስት፥ እርሱ ወደ ጕድጓዱ ይወድቃል፤ ፍጹማን ግን መልካም ነገርን ይወርሳሉ።
- 11
ባለጠጋ ሰው ለራሱ ጠቢብ የሆነ ይመስለዋል፤ አስተዋይ ድሀ ግን ይመረምረዋል።
- 12
ጻድቃን ድል ባደረጉ ጊዜ ብዙ ክብር አለ፤ ኀጥኣን ከፍ ከፍ ባሉ ጊዜ ግን ሰው ይሸሸጋል።
- 13
ኃጢአቱን የሚሰውር አይለማም፤ የሚናዘዝባትና የሚተዋት ግን ምሕረትን ያገኛል።
- 14
ሁልጊዜ የሚፈራ ሰው ምስጉን ነው፤ ልቡን የሚያጸና ግን በክፉ ላይ ይወድቃል።
- 15
በድሀ ሕዝብ ላይ የሚገዛ ክፉ መኰንን እንደሚያገሣ አንበሳን እንደ ተራበ ድብ ነው።
- 16
አእምሮ የጐደለው መኰንን ትልቅ ግፈኛ ነው፤ ግፍን የሚጠላ ግን ብዙ ዘመን ይኖራል።
- 17
የሰው ደም ያለበት ሰው እንደ ጕድጓድ ይሸሻል፥ ማንም አያስጠጋውም።
- 18
በቅንነት የሚሄድ ይድናል፤ በጠማምነት የሚሄድ ግን ወዲያው ይወድቃል።
- 19
ምድሩን የሚያርስ እንጀራ ይጠግባል፤ ምናምንቴዎችን የሚከተል ግን ድህነት ይሞላበታል።
- 20
የታመነ ሰው እጅግ ይባረካል፤ ባለጠጋ ለመሆን የሚቸኵል ግን ሳይቀጣ አይቀርም።
- 21
ማድላት፥ በቍራሽ እንጀራም መበደል መልካም አይደለም።
- 22
ምቀኛ ሰው ባለጠጋ ለመሆን ይቸኵላል ችጋርም እንደሚመጣበት አያውቅም።
- 23
ምላሱን ከሚያጣፍጥ ይልቅ ሰውን የሚገሥጽ በኋላ ሞገስ ያገኛል።
- 24
ከአባቱና ከእናቱ የሚሰርቅ። ኃጢአትን አልሠራሁም የሚልም የአጥፊ ባልንጀራ ነው።
- 25
የሚጐመጅ ሰው ክርክርን ያነሣሣል፤ በእግዚአብሔር የሚታመን ግን ይጠግባል።
- 26
በገዛ ልቡ የሚታመን ሰው ሰነፍ ነው፤ በጥበብ የሚሄድ ግን ይድናል።
- 27
ለድሀ የሚሰጥ አያጣም፤ ዓይኖቹን የሚጨፍን ግን እጅግ ይረገማል።
- 28
ኀጥአን በተነሡ ጊዜ ሰዎች ይሸሸጋሉ፤ እነርሱ በጠፉ ጊዜ ግን ጻድቃን ይበዛሉ።