Proverbs 18
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
መለየት የሚወድድ ምኞቱን ይከተላል፥ መልካሙንም ጥበብ ሁሉ ይቃወማል።
- 2
ሰነፍ የጥበብን ነገር አይወድድም፤ በልቡ ያለውን ሁሉ መግለጥ ብቻ ይወድዳል እንጂ።
- 3
ኀጥእ በመጣ ጊዜ ንቀት ደግሞ ይመጣል፥ ነውርም ከስድብ ጋር።
- 4
የሰው አፍ ቃል የጠለቀ ውኃ ነው፥ የጥበብም ምንጭ ፈሳሽ ወንዝ ነው።
- 5
የጻድቅ ፍርድ ይጠምም ዘንድ፥ ለኀጥእም ማድላት መልካም አይደለም።
- 6
የሰነፍ ከንፈር በጥል ውስጥ ትገባለች፥ አፉም በትርን ትጠራለች።
- 7
የሰነፍ አፍ ለራሱ ጥፋት ነው፥ ከንፈሩም ለነፍሱ ወጥመድ ነው።
- 8
የጆሮ ጠቢ ቃል እንደ ጣፋጭ መብል ነው፥ እርሱም እስከ ሆድ ጕርጆች ድረስ ይወርዳል።
- 9
በሥራው ታካች የሚሆን የሀብት አጥፊ ወንድም ነው።
- 10
የእግዚአብሔር ስም የጸና ግምብ ነው፤ ጻድቅ ወደ እርሱ ሮጦ ከፍ ከፍ ይላል።
- 11
ለባለጠጋ ሰው ሀብቱ እንደ ጸናች ከተማ ናት፥ በአሳቡም እንደ ረጅም ቅጥር።
- 12
ሰው ሳይወድቅ በፊት ልቡ ከፍ ከፍ ይላል፥ ትሕትናም ክብረትን ትቀድማለች።
- 13
ሳይሰማ ነገርን በሚመልስ ስንፍናና እፍረት ይሆንበታል።
- 14
የሰው ነፍስ ሕመሙን ይታገሣል፤ የተቀጠቀጠን መንፈስ ግን ማን ያጠንክረዋል?
- 15
የአስተዋይ ልብ እውቀትን ያገኛል፥ የጠቢባንም ጆሮ እውቀትን ትፈልጋለች።
- 16
የሰው ስጦታ መንገዱን ታሰፋለታለች፥ በታላላቆችም ፊት ታገባዋለች።
- 17
ወደ ፍርድ አስቀድሞ የገባ ጻድቅ ይመስላል፤ ባልንጀራው ግን መጥቶ ይመረምረዋል።
- 18
ዕጣ ክርክርን ትከለክላለች፥ በኃያላንም መካከል ትበይናለች።
- 19
የተበደለ ወንድም እንደ ጸናች ከተማ ጽኑ ነው፤ ክርክራቸውም እንደ ግንብ ብረት ነው።
- 20
የሰው ሆድ ከአፉ ፍሬ ይሞላል ከንፈሩም ከሚያፈራው ይጠግባል።
- 21
ሞትና ሕይወት በምላስ እጅ ናቸው፤ የሚወድዱአትም ፍሬዋን ይበላሉ።
- 22
ሚስት ያገኘ በረከትን አገኘ፥ ከእግዚአብሔርም ሞገስን ይቀበላል።
- 23
ድሀ በትሕትና እየለመነ ይናገራል፤ ባለጠጋ ግን በድፍረት ይመልሳል።
- 24
ብዙ ወዳጆች ያሉት ሰው ይጠፋል፤ ነገር ግን ከወንድም አብልጦ የሚጠጋጋ ወዳጅ አለ።