Proverbs 16
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
የልብ መዘጋጀት ከሰው ነው፤ የምላስ መልስ ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው።
- 2
የሰው መንገድ ሁሉ በዓይኖቹ ፊት ንጹሕ ነው፤ እግዚአብሔር ግን መንፈስን ይመዝናል።
- 3
ሥራህን ለእግዚአብሔር አደራ ስጥ፥ አሳብህም ትጸናለች።
- 4
እግዚአብሔር ሁሉን ለእርሱ ለራሱ ፈጠረ፥ ኀጥእን ደግሞ ለክፉ ቀን።
- 5
በልቡ የታበየ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ ርኩስ ነው፥ እጅ በእጅም ሳይቀጣ አይቀርም።
- 6
በምሕረትና በእውነት ኃጢአት ትሰረያለች፥ እግዚአብሔርንም በመፍራት ሰው ከክፋት ይመለሳል።
- 7
የሰው አካሄድ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘው እንደ ሆነ፤ በእርሱና በጠላቶቹ መካከል ስንኳ ሰላምን ያደርጋል።
- 8
በጽድቅ የሚገኝ ጥቂት ነገር በዓመፅ ከሚገኝ ከብዙ ትርፍ ይሻላል።
- 9
የሰው ልብ መንገዱ ያዘጋጃል፤ እግዚአብሔር ግን አካሄዱን ያቀናለታል።
- 10
የእግዚአብሔር ብይን በንጉሥ አፍ ነው፥ አፉም በፍርድ አይስትም።
- 11
እውነተኛ ሚዛንና መመዘኛ የእግዚአብሔር ናቸው፤ የከረጢት መመዘኛዎች ሁሉ የእርሱ ሥራ ናቸው።
- 12
ግፍን መሥራት በንጉሥ ዘንድ ጸያፍ ነገር ነው፥ ዙፋን በጽድቅ ይጸናልና።
- 13
የጽድቅ ከንፈር የነገሥታት ደስታ ናት፥ በቅን የሚናገር እርሱንም ይወድዱታል።
- 14
የንጉሥ ቍጣ እንደ ሞት መልእክተኛ ነው፤ ጠቢብ ሰው ግን ያቈላምጠዋል።
- 15
በንጉሥ ፊት ብርሃን ዘንድ ሕይወት አለ፥ መልካም ፈቃዱም እንደ በልግ ዝናብ ደመና ነው።
- 16
ጥበብን ማግኘት ምንኛ ከወርቅ ይሻላል! ማስተዋልንም ማግኘት ከብር ይልቅ የሚመረጥ ነው።
- 17
የቅኖች መንገድ ከክፋት መራቅ ነው፤ መንገዱን የሚጠብቅ ነፍሱን ይጠብቃታል።
- 18
ትዕቢት ጥፋትን፥ ኵሩ መንፈስም ውድቀትን ይቀድማል።
- 19
ከዕቡያን ጋር ምርኮ ከመካፈል ከትሑታን ጋር በተዋረደ መንፈስ መሆን ይሻላል።
- 20
ቃልን የሚያዳምጥ መልካም ነገርን ያገኛል፤ በእግዚአብሔር የታመነ ምስጉን ነው።
- 21
ልቡ ጠቢብ የሆነ አስተዋይ ይባላል፥ በከንፈሩም ጣፋጭ የሆነ ትምህርትን ያበዛል።
- 22
ገንዘብ ላደረገው ሰው እውቀት የሕይወት ምንጭ ነው፤ ስንፍና ግን የሰነፎች ቅጣት ነው።
- 23
የጠቢብ ልብ አፉን ያስተምራል፥ ለከንፈሩም ትምህርትን ይጨምራል።
- 24
ያማረ ቃል የማር ወለላ ነው፤ ለነፍስ ጣፋጭ ለአጥንትም ጤና ነው።
- 25
ለሰው ቅን የምትመስል መንገድ አለች፤ ፍጻሜዋ ግን የሞት መንገድ ነው።
- 26
የሠራተኛ ራብ ለእርሱ ይሠራል፥ አፉ ይጐተጕተዋልና።
- 27
ምናምንቴ ሰው ክፋትን ይምሳል፥ በከንፈሩም የሚቃጠል እሳት አለ።
- 28
ጠማማ ሰው ጥልን ይዘራል፤ ጆሮ ጠቢ ሰው የተማመኑትን ወዳጆች ይለያያል።
- 29
ግፈኛ ሰው ወዳጁን ያባብላል፥ መልካምም ወዳይደለ መንገድ ይመራዋል።
- 30
ዓይኑን የሚዘጋ ጠማማ አሳብን ያስባል፤ ከንፈሩን የሚነክስ ክፋትን ይፈጽማል።
- 31
የሸበተ ጠጕር የክብር ዘውድ ነው፥ እርሱም በጽድቅ መንገድ ይገኛል።
- 32
ትዕግሥተኛ ሰው ከኃያል ሰው ይሻላል፥ በመንፈሱም ላይ የሚገዛ ከተማ ከሚወስዱ ይበልጣል።
- 33
ዕጣ በጕያ ይጣላል፤ መደብዋ ሁሉ ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው።