Proverbs 13
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
ባለ አእምሮ ልጅ የአባቱን ተግሣጽ ይሰማል። ፌዘኛ ግን ተግሣጽን አይሰማም።
- 2
ሰው ከአፉ ፍሬ መልካምን ይበላል፤ የዓመፀኞች ነፍስ ግን ግፍን ትሻለች።
- 3
አፉን የሚጠብቅ ነፍሱን ይጠብቃል፤ ከንፈሩን የሚያሞጠሙጥ ግን ጥፋትን ያገኘዋል።
- 4
የታካች ሰው ነፍስ ትመኛለች፤ አንዳችም አታገኝም፤ የትጉ ነፍስ ግን ትጠግባለች።
- 5
ጻድቅ ሐሰትን ይጠላል፤ ኀጥእ ግን ያሳፍራል ያስነውራልም።
- 6
በመንገዱ ያለ ነውር የሚሄደውን ጽድቅ ይጠብቀዋል፤ ኃጢአት ግን ኃጢአተኛውን ይጥለዋል።
- 7
ራሱን ባለጠጋ የሚያስመስል ሰው አለ፥ ነገር ግን አንዳች የለውም፤ ራሱን ድሀ የሚያስመስል አለ፥ ነገር ግን እጅግ ባለጠግነት አለው።
- 8
ለሰው ነፍስ ቤዛው ሀብቱ ነው፤ ድሀ ግን ተግሣጽን አይሰማም።
- 9
ሁልጊዜ ለጻድቃን ብርሃን ነው፤ የኀጥኣን መብራት ግን ይጠፋል።
- 10
በትዕቢት ጠብ ብቻ ይሆናል፤ ጥበብ ግን ምክርን በሚቀበሉ ዘንድ ናት።
- 11
በችኰላ የምትከማች ሀብት ትጐድላለች፤ ጥቂት በጥቂት የተከማቸች ግን ትበዛለች።
- 12
የምትዘገይ ተስፋ ልብን ታሳዝናለች፤ የተገኘች ፈቃድ ግን የሕይወት ዛፍ ናት።
- 13
ትእዛዝን የሚያቃልል በትእዛዝ ተይዞ ይጠፋል፤ ትእዛዝን የሚፈራ ግን በደኅንነት ይኖራል።
- 14
ሰው ከሞት ወጥመድ ያመልጥ ዘንድ የጠቢብ ሰው ትምህርት የሕይወት ምንጭ ነው።
- 15
መልካም እውቀት ሞገስን ይሰጣል፤ የወስላቶች መንገድ ግን ሸካራ ናት።
- 16
ብልህ ሁሉ በእውቀት ይሠራል፤ ሰነፍ ግን ስንፍናውን ይገልጣል።
- 17
መጥፎ መልእክተኛ በክፉ ላይ ይወድቃል፤ የታመነ መልእክተኛ ግን ፈውስ ነው።
- 18
ድህነትና ነውር ተግሣጽን ቸል ለሚሉ ነው፤ ዘለፋን የሚሰማ ግን ይከብራል።
- 19
የተፈጸመች ፈቃድ ሰውነትን ደስ ታሰኛለች፤ ሰነፎች ግን ከክፉ መራቅን ይጸየፋሉ።
- 20
ከጠቢባን ጋር የሚሄዱ ጠቢብ ይሆናል፤ የሰነፎች ባልንጀራ ግን ክፉ መከራን ይቀበላል።
- 21
ክፉ ነገር ኃጢአተኞችን ያሳድዳቸዋል፤ ጻድቃን ግን መልካሙን ዋጋ ይቀበላሉ።
- 22
ጻድቅ ሰው ለልጅ ልጆቹ ያወርሳል፤ የኃጢአተኛ ብልጥግና ግን ለጻድቅ ትጠበቃለች።
- 23
በድሆች እርሻ ላይ ብዙ ሲሳይ አለ፤ ከፍርድ መጕደል የተነሣ ግን ይጠፋል።
- 24
በበትር ከመምታት የሚራራ ሰው ልጁን ይጠላል፤ ልጁን የሚወድድ ግን ተግቶ ይገሥጻዋል።
- 25
ጻድቅ ሰውነቱ እስክትጠግብ ድረስ ይበላል፤ የኀጥኣን ሆድ ግን ይራባል።