Nehemiah 3
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
ታላቁም ካህን ኤልያሴብ ወንድሞቹም ካህናት ተነሥተው የበግ በር ሠሩ፤ ቀደሱትም፥ ሳንቃዎቹንም አቆሙ፤ እስከ ሃሜአ ግንብና እስከ ሐናንኤል ግንብ ድረስ ቀደሱት።
- 2
በአጠገቡ የኢያሪኮ ሰዎች ሠሩ፤ በአጠገባቸውም የአምሪ ልጅ ዘኩር ሠራ።
- 3
የሃስናአ ልጆችም የዓሣ በር ሠሩ፤ ሰረገሎቹን አኖሩ፥ ሳንቃዎቹንም አቆሙ፥ ቍልፎቹንና መወርወሪያዎቹንም አደረጉ።
- 4
በአጠገባቸውም የአቆስ ልጅ የኦርዮ ልጅ ሜሪሞት አደሰ። በአጠገባቸውም የሜሴዜቤል ልጅ የበራክያ ልጅ ሜሱላም አደሰ። በአጠገባቸውም የበዓና ልጅ ሳዶቅ አደሰ።
- 5
በአጠገባቸውም ቴቁሐውያን አደሱ፤ ታላላቆቻቸው ግን ለጌታቸው ሥራ አንገታቸውን አላዋረዱም።
- 6
የፋሴሐ ልጅ ዮዳሄና የበሶድያ ልጅ ሜሱላም አሮጌውን በር አደሱ፤ ሰረገሎቹን አኖሩ፥ ሳንቃዎቹንም አቆሙ፥ ቍልፎቹንና መወርወሪያዎቹንም አደረጉ።
- 7
በአጠገባቸውም ገባዖናዊው መልጥያና ሜሮኖታዊው ያዶን፥ የወንዙም ማዶ አለቃ ግዛት የሆኑ የገባዖንና የምጽጳ ሰዎች አደሱ።
- 8
በአጠገባቸውም ወርቅ አንጥረኛው የሐርሃያ ልጅ ዑዝኤል አደሰ። በአጠገቡም ከሽቱ ቀማሚዎች የነበረ ሐናንያ አደሰ፤ እስከ ሰፊው ቅጥር ድረስ ኢየሩሳሌምን ጠገኑ።
- 9
በአጠገባቸውም የኢየሩሳሌም ግዛት እኵሌታ አለቃ የሆር ልጅ ረፋያ አደሰ።
- 10
በአጠገባቸውም የኤርማፍ ልጅ ይዳያ በቤቱ አንጻር ያለውን አደሰ። በአጠገቡም የአሰበንያ ልጅ ሐጡስ አደሰ።
- 11
የካሪም ልጅ መልክያ፥ የፈሐት ሞዓብ ልጅም አሱብ ሌላውን ክፍልና የእቶኑን ግንብ አደሱ።
- 12
በአጠገባቸውም የኢየሩሳሌም ግዛት እኵሌታና የመንደሮችዋ አለቃ የአሎኤስ ልጅ ሰሎም አደሰ።
- 13
ሐኖንና የዛኖዋ ሰዎችም የሸለቆውን በር አደሱ፤ ሠሩት፥ ሳንቃዎቹንም አቆሙ፥ ቍልፎቹንና መወርወሪያዎቹንም አደረጉ፤ ደግሞም እስከ ጕድፍ መጣያው በር ድረስ አንድ ሺህ ክንድ የሚሆን ቅጥር ሠሩ።
- 14
የቤትሐካሪምም ግዛት አለቃ የሬካብ ልጅ መልክያ የጕድፍ መጣያውን በር አደሰ፤ ሠራው፥ ሳንቃዎቹንም አቆመ፥ ቍልፎቹንና መወርወሪያዎቹንም አደረገ።
- 15
የምጽጳም ግዛት አለቃ የኮልሖዜ ልጅ ሰሎም የምንጩን በር አደሰ፤ ሠራው፥ ከደነውም፥ ሳንቃዎቹንም አቆመ፥ ቍልፎቹንና መወርወሪያዎቹንም አደረገ፤ ከዳዊትም ከተማ እስከሚወርደው ደረጃ ድረስ በንጉሡ አትክልት አጠገብ ያለውን የሼላን መዋኛ ቅጥር ሠራ።
- 16
ከእርሱም በኋላ የቤትጹር ግዛት እኵሌታ አለቃ የዓዝቡቅ ልጅ ነህምያ በዳዊት መቃብር አንጻር እስካለው ስፍራ፥ እስከ ተሠራውም መዋኛ፥ እስከ ኃያላኑም ቤት ድረስ አደሰ።
- 17
ከእርሱም በኋላ ሌዋውያንና የባኒ ልጅ ሬሁም አደሱ። በአጠገባቸውም የቅዒላ ግዛት እኵሌታ አለቃ ሐሸብያ ስለ ግዛቱ አደሰ።
- 18
ከእርሱም በኋላ የቅዒላ ግዛት እኵሌታ አለቃ የኤንሐዳድ ልጅ በዋይ ወንድሞቹም አደሱ።
- 19
በአጠገቡም የምጽጳ አለቃ የኢያሱ ልጅ ኤጽር በማዕዘኑ አጠገብ በጦር መሣሪያ ቤት አንጻር ሌላውን ክፍል አደሰ።
- 20
ከእርሱም በኋላ የዘባይ ልጅ ባሮክ ከማዕዘኑ ጀምሮ እስከ ታላቁ ካህን እስከ ኤልያሴብ ቤት መግቢያ ድረስ ሌላውን ክፍል ተግቶ አደሰ።
- 21
ከእርሱም በኋላ የአቆስ ልጅ የኦርዮ ልጅ ሜሪሞት ከኤልያሴብ ቤት መግቢያ ጀምሮ እስከ ኤልያሴብ ቤት መጨረሻ ድረስ ሌላውን ክፍል አደሰ።
- 22
ከእርሱም በኋላ የቈላው ሰዎች ካህናቱ አደሱ።
- 23
ከእነርሱም በኋላ ብንያምና አሱብ በቤታቸው አንጻር ያለውን አደሱ። ከእነርሱም በኋላ የሐናንያ ልጅ የመዕሤያ ልጅ ዓዛርያስ በቤቱ አጠገብ ያለውን አደሰ።
- 24
ከእርሱም በኋላ የኤንሐደድ ልጅ ቢንዊ ከዓዛርያስ ቤት ጀምሮ እስከ ማዕዘኑ ድረስ ሌላውን ክፍል አደሰ።
- 25
የኡዛይ ልጅ ፋላል በማዕዘኑ አንጻር ያለውንና በዘበኞች አደባባይ አጠገብ ከላይኛው የንጉሡ ቤት ወጥቶ የቆመውን ግንብ ሠራ። ከእርሱም በኋላ የፋሮስ ልጅ ፈዳያ ሠራ።
- 26
ናታኒምም በዖፌል በውኃው በር አንጻር በምሥራቅ በኩል ወጥቶ በቆመው ግንብ አጠገብ እስካለው ስፍራ ድረስ ተቀመጡ።
- 27
ከእርሱም በኋላ ቴቁሐውያን ወጥቶ በቆመው በታላቁ ግንብ አንጻር ያለውን እስከ ዖፌል ቅጥር ድረስ ሌላውን ክፍል አደሱ።
- 28
ከፈረሱ በር በላይ ካህናቱ እያንዳንዳቸው በየቤታቸው አንጻር አደሱ።
- 29
ከዚያ በኋላ የኢሜር ልጅ ሳዶቅ በቤቱ አንጻር አደሰ። ከእርሱም በኋላ የምሥራቁን በር ጠባቂ የሴኬንያ ልጅ ሸማያ አደሰ።
- 30
ከእርሱ በኋላ የሰሌምያ ልጅ ሐናንያና የሴሌፍ ስድስተኛው ልጁ ሐኖን ሌላውን ክፍል አደሱ። ከዚያም በኋላ የበራክያ ልጅ ሜሱላም በጓዳው አንጻር ያለውን አደሰ።
- 31
ከእርሱም በኋላ ከወርቅ አንጥረኞቹ የነበረ መልክያ እስከ ናታኒምና እስከ ነጋዴዎቹ ቤት ድረስ በሐሚፍቃድ በር አንጻር ያለውን እስከ ማዕዘኑ መውጫ ድረስ አደሰ።
- 32
ከማዕዘኑም መውጫ ጀምረው እስከ በጉ በር ድረስ ወርቅ አንጥረኞችና ነጋዴዎች አደሱ።