Micah 6
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
አሁን። ተነሣ፥ በተራሮችም ፊት ተፋረድ፥ ኮረብቶችም ቃልህን ይስሙ ብሎ እግዚአብሔር የሚለውን ስሙ።
- 2
ተራሮች ሆይ፥ ጠንካሮች የምድር መሠረቶችም ሆይ፥ እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር ክርክር አለውና፥ ከእስራኤልም ጋር ይፋረዳልና የእግዚአብሔርን ክርክር ስሙ።
- 3
ሕዝቤ ሆይ፥ ምን አድርጌሃለሁ? በምንስ አድክሜሃለሁ? መስክርብኝ።
- 4
ከግብጽ ምድር አውጥቼሃለሁ፥ ከባርነት ቤትም ተቤዥቼሃለሁ፤ በፊትህም ሙሴንና አሮንን ማርያምንም ልኬልህ ነበር።
- 5
ሕዝቤ ሆይ፥ የሞዓብ ንጉሥ ባላቅ የመከረውን፥ የቢዖርም ልጅ በለዓም የመለሰለትን አሁን አስብ፤ የእግዚአብሔርንም የጽድቅ ሥራ ታውቅ ዘንድ ከሰጢም ጀምሮ እስከ ጌልገላ ድረስ አስብ።
- 6
ምን ይዤ ወደ እግዚአብሔር ፊት ልምጣና በልዑል አምላክ ፊት ልስገድ? የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የአንዱን ዓመት ጥጃ ይዤ በፊቱ ልምጣን?
- 7
እግዚአብሔርስ በሺህ አውራ በጎች ወይስ በእልፍ የዘይት ፈሳሾች ደስ ይለዋልን? ወይስ የበኵር ልጄን ስለ በደሌ፥ የሆዴንም ፍሬ ስለ ነፍሴ ኃጢአት እሰጣለሁን?
- 8
ሰው ሆይ፥ መልካሙን ነግሮሃል፤ እግዚአብሔርም ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው? ፍርድን ታደርግ ዘንድ፥ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፥ ከአምላክህም ጋር በትሕትና ትሄድ ዘንድ አይደለምን?
- 9
የእግዚአብሔር ድምፅ ከተማይቱን ይጠራታል፤ ስምህን መፍራት ጥበብ ነው፤ የመቅሠፍትን በትር፥ እርሱንም ያዘጋጀ ማን እንደ ሆነ ስሙ።
- 10
በውኑ በኃጢአተኛ ቤት የኃጢአት መዝገብ፥ የተጸየፈም ውሽተኛ መስፈሪያ ገና አለ ይሆን?
- 11
በአባይ ሚዛንና በከረጢት ባለ በተንኰል መመዘኛ ንጹሕ እሆናለሁን?
- 12
ባለ ጠጎችዋን ግፍ ሞልቶባቸዋል፤ በእርስዋም የሚኖሩ በሐሰት ተናግረዋል፥ ምላሳቸውም በአፋቸው ውስጥ ተንኰለኛ ነው።
- 13
ስለዚህ እኔ ደግሞ በክፉ ቍስል መታሁህ፤ ስለ ኃጢአትህም አፈርስሁህ።
- 14
ትበላለህ፥ ነገር ግን አትጠግብም፥ ችጋርህም በመካከልህ ይሆናል፤ ትወስዳለህ፥ ነገር ግን አታድንም፤ የምታድነውንም ለሰይፍ እሰጣለሁ።
- 15
ትዘራለህ፥ ነገር ግን አታጭድም፤ ወይራውንም ትጨምቃለህ፥ ነገር ግን ዘይቱን አትቀባም፤ ወይኑንም ትጨምቃለህ፥ ነገር ግን የወይን ጠጁን አትጠጣም።
- 16
አንተን ለጥፋት፥ በእርስዋም የሚኖሩትን ለማፍዋጫ እሰጥ ዘንድ የዘንበሪን ሥርዓትና የአክዓብን ቤት ሥራ ሁሉ ጠብቃችኋል፥ በምክራቸውም ሄዳችኋል፤ የሕዝቤንም ስድብ ትሸከማላችሁ።<br />