Micah 4
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
በመጨረሻውም ዘመን የእግዚአብሔር ቤት ተራራ በተራሮች ራስ ላይ ጸንቶ ይቆማል፥ ከኮረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላል፤ አሕዛብም ወደ እርሱ ይጐርፋሉ።
- 2
ከጽዮን ሕግ፥ ከኢየሩሳሌምም የእግዚአብሔር ቃል ይወጣልና ብዙዎች አሕዛብ ሄደው። ኑ፥ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፥ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል፥ በፍለጋውም እንሄዳለን ይላሉ።
- 3
በብዙዎችም አሕዛብ መካከል ይፈርዳል፥ በሩቅም ባሉ በብርቱዎች አሕዛብ ላይ ይበይናል፤ ሰይፋቸውንም ማረሻ፥ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፤ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም ከእንግዲህም ወዲህ ሰልፍ አይማሩም።
- 4
የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር አፍም ተናግሮአልና ሰው እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ይቀመጣል፥ የሚያስፈራውም የለም።
- 5
ሕዝብም ሁሉ እያንዳንዱ በየአምላኩ ስም ይሄዳል፥ እኛም በአምላካችን በእግዚአብሔር ስም ለዘላለም እንሄዳለን።
- 6
በዚያ ቀን አንካሳይቱን እሰበስባለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ የባከነችውንና ያስጨነቅኋትንም አከማቻለሁ፤
- 7
አንካሳይቱንም ለቅሬታ፥ ወደ ሩቅም የተጣለችውን ለብርቱ ሕዝብ አደርጋታለሁ፤ ከዚያም ወዲያ እስከ ዘላለም ድረስ እግዚአብሔር በጽዮን ተራራ በእነርሱ ላይ ይነግሣል።
- 8
አንተም የመንጋ ግንብ ሆይ፥ የጽዮን ሴት ልጅ አምባ፥ ወደ አንተ ትመጣለች፤ የቀደመችው ግዛት፥ የኢየሩሳሌም ሴት ልጅ መንግሥት ትደርሳለች።
- 9
አሁንስ ለምን ትጮኺአለሽ? እንደምትወልድ ሴት ምጥ የደረሰብሽ፥ ንጉሥ ስለሌለሽ ነውን? ወይስ መካሪ ስለ ጠፋብሽ ነውን?
- 10
የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እንደምትወልድ ሴት አምጠሽ ውለጂ፤ አሁን ከከተማ ትወጫለሽና፥ በሜዳም ትቀመጫለሽ፥ ወደ ባቢሎንም ትደርሻለሽ፤ በዚያም ያድንሻል፥ በዚያም እግዚአብሔር ከጠላቶችሽ እጅ ይቤዥሻል።
- 11
አሁንም። ርኩስ ትሁን፥ ዓይናችንም በጽዮን ላይ ይይ የሚሉ ብዙ አሕዛብ በአንቺ ላይ ተሰብስበዋል።
- 12
ነገር ግን የእግዚአብሔርን አሳብ አያውቁም፥ ምክሩንም አያስተውሉም፤ እንደ ነዶ ወደ አውድማ አከማችቶአቸዋልና።
- 13
የጽዮን ልጅ ሆይ፥ ቀንድሽን ብረት፥ ጥፍርሽንም ናስ አደርጋለሁና ተነሺ አሂጂ፤ ብዙ አሕዛብንም ታደቅቂአለሽ፤ ትርፋቸውንም ለእግዚአብሔር፥ ሀብታቸውንም ለምድር ሁሉ ጌታ ትቀድሻለሽ።