Leviticus 25
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
እግዚአብሔርም ሙሴን በሲና ተራራ ላይ እንዲህ ብሎ ተናገረው።
- 2
ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። እኔ ወደምሰጣችሁ ምድር በገባችሁ ጊዜ ምድሪቱ ለእግዚአብሔር ሰንበት ታድርግ።
- 3
ስድስት ዓመት እርሻህን ዝራ፥ ስድስት ዓመትም ወይንህን ቍረጥ ፍሬዋንም አግባ።
- 4
በሰባተኛው ዓመት ግን ለምድሪቱ የዕረፍት ሰንበት፥ ለእግዚአብሔር ሰንበት፥ ትሁን፤ እርሻህን አትዝራ፥ ወይንህንም አትቍረጥ።
- 5
የምድራችሁን የገቦ አትጨደው፥ ያልተቈረጠውንም የወይንህን ፍሬ አታከማች፤ ለምድሪቱ የዕረፍት ሰንበት ዓመት ይሁን።
- 6
የምድርም ሰንበት ለአንተ፥ ለወንድ ባሪያህም፥ ለሴት ባሪያህም፥ ለምንደኛውም፥ ከአንተ ጋር ለሚኖር ለመጻተኛም ምግብ ይሁን።
- 7
ለእንስሶችህም፥ በምድርህም ላሉት አራዊት ፍሬዋ ሁሉ መኖ ይሁን።
- 8
ሰባት ጊዜ ሰባት አድርገህ የዓመታትን ሰንበት ሰባት ቍጠር፤ የሰባት ዓመታትም ሰንበት ዘመን አርባ ዘጠኝ ዓመት ትቈጥራለህ።
- 9
ከዚያም በኋላ በሰባተኛው ወር በአሥረኛው ቀን በቀንደ መለከት ታውጃለህ፤ በማስተስረያ ቀን በምድራችሁ ሁሉ በቀንደ መለከት ታውጃላችሁ።
- 10
አምሳኛውንም ዓመት ትቀድሳላችሁ፥ በምድሪቱም ለሚኖሩባት ሁሉ ነጻነትን ታውጃላችሁ፤ እርሱ ለእናንተ ኢዮቤልዩ ነው፤ ሰው ሁሉ ወደ ርስቱና ወደ ወገኑ ይመለስ።
- 11
ያ አምሳኛው ዓመት ለእናንተ ኢዮቤልዩ ይሆናል፤ በእርሱም አትዝሩ፥ የገቦውንም አትጨዱ፥ የወይኑንም ፍሬ አታከማቹ።
- 12
ኢዮቤልዩ ነውና የተቀደሰ ይሁንላችሁ፤ በሜዳ ላይ የበቀለውን ብሉ።
- 13
በዚች በኢዮቤልዩ ዓመት ሰው ሁሉ ወደ ርስቱ ይመለሳል።
- 14
ለባልንጀራህም አንዳች ብትሸጥለት፥ ወይም ከባልንጀራህ እጅ ብትገዛ፥ ሰው ባልንጀራውን አያታልል።
- 15
ከኢዮቤልዩ በኋላ እንደ ዓመታቱ ቍጥር ከባልንጀራህ ትገዛለህ፤ እርሱም እንደ መከሩ ዓመታት ቍጥር ይሸጥልሃል።
- 16
እንደ ዓመታቱ ብዛት ዋጋውን ታበዛለህ፥ እንደ ዓመታቱም ማነስ ዋጋውን ታሳንሳለህ፤ እንደ መከሩ ቍጥር ይሸጥልሃል።
- 17
እኔም እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና ሰው ባልንጀራውን አያታልል፥ ነገር ግን አምላክህን ፍራ።
- 18
ሥርዓቴንም አድርጉ፥ ፍርዶቼንም ጠብቁ አድርጉትም፤ በምድሪቱም ውስጥ በጸጥታ ትኖራላችሁ።
- 19
ምድሪቱም ፍሬዋን ትሰጣለች፥ እስክትጠግቡም ድረስ ትበላላችሁ፤ በእርስዋም ውስጥ በጸጥታ ትኖራላችሁ።
- 20
እናንተም። ካልዘራን፥ እህላችንንም ካላከማቸን በሰባተኛው ዓመት ምን እንበላለን? ብትሉ፥
- 21
እኔ በስድስተኛው ዓመት በረከቴን በላያችሁ አዝዛለሁ፤ ምድሪቱም የሦስት ዓመት ፍሬ ታፈራለች።
- 22
በስምንተኛውም ዓመት ትዘራላችሁ፥ ከአሮጌውም እህል ትበላላችሁ፤ ፍሬዋ እስኪገባ፥ እስከ ዘጠነኛው ዓመት ድረስ፥ ከአሮጌው እህል ትበላላችሁ።
- 23
ምድርም ለእኔ ናትና፥ እናንተም ከእኔ ጋር እንግዶችና መጻተኞች ናችሁና ምድርን ለዘላለም አትሽጡ።
- 24
በርስታችሁም ምድር ሁሉ መቤዠትን ለምድሪቱ አድርጉ።
- 25
ወንድምህም ቢደኸይ ከርስቱም ቢሸጥ፥ ለእርሱ የቀረበ ዘመዱ መጥቶ ወንድሙ የሸጠውን ይቤዠዋል።
- 26
የሚቤዠውም ሰው ቢያጣ፥ እርሱም እጁ ቢረጥብ፥ ለመቤዠትም የሚበቃ ቢያገኝ፥
- 27
የሽያጩን ዘመን ቈጥሮ የቀረውን ወደ ገዛው ሰው ይመልስ፤ እርሱም ወደ ርስቱ ይመለስ።
- 28
ለራሱም ዕዳውን መክፈል ባይችል፥ ሽያጩ በገዛው ሰው እጅ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ይቀመጥ፤ በኢዮቤልዩም ዓመት ይውጣ፥ እርሱም ወደ ርስቱ ይመለስ።
- 29
ሰውም ቅጥር ባለበት ከተማ መኖሪያ ቤትን ቢሸጥ፥ ከተሸጠ በኋላ አንድ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ ለመቤዠት ይችላል፤ ለአንድ ሙሉ ዓመት መቤዠት ይችላል።
- 30
አንድ ዓመትም እስኪጨረስ ባይቤዠው፥ ቅጥር ባለበት ከተማ የሚሆን ቤት ለገዛው ለልጅ ልጁ ለዘላለም ይጸናለታል፤ በኢዮቤልዩም ከእርሱ አይወጣም።
- 31
ቅጥር በሌለበት መንደር ያሉ ቤቶች ግን እንደ እርሻ ይቈጠራሉ፤ ይቤዣሉ፥ በኢዮቤልዩም ይወጣሉ።
- 32
በእነርሱ ከተማ ያለ የሌዋውያን ቤት ግን ሌዋውያን ለዘላለም መቤዠት ይችላሉ።
- 33
ማናቸውም ሰው ከሌዋውያን ቢገዛ፥ በእስራኤል ልጆች መካከል የሌዋውያን ከተማ ቤቶች ርስቶቻቸው ናቸውና በርስቱ ከተማ ያለ የተሸጠው ቤት በኢዮቤልዩ ይመለሳል።
- 34
በከተማቸውም ዙሪያ ያለችው መሰምርያ የዘላለም ርስታቸው ናትና አትሸጥም።
- 35
ወንድምህ ቢደኸይ እጁም በአንተ ዘንድ ቢደክም፥ አጽናው፤ እንደ እንግዳና እንደ መጻተኛም ከአንተ ጋር ይኑር።
- 36
ወንድምህ ከአንተ ጋር ይኖር ዘንድ ከእርሱ ምንም ወለድ ወይም ትርፍ አትውሰድ፤ ነገር ግን አምላክህን ፍራ።
- 37
ብርህን በወለድ አታበድረው፤ መኖህንም በትርፍ አትስጠው።
- 38
የከነዓንን ምድር እሰጣችሁ ዘንድ፥ አምላክም እሆናችሁ ዘንድ ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።
- 39
ወንድምህም ቢደኸይ ራሱንም ለአንተ ቢሸጥ፥ እንደ ባሪያ አድርገህ አትግዛው።
- 40
እንደ ምንደኛና እንደ መጻተኛ ከአንተ ጋር ይሁን፤ እስከ ኢዮቤልዩም ዓመት ያገልግልህ።
- 41
በዚያን ጊዜም እርሱ ከልጆቹ ጋር ከአንተ ይውጣ፥ ወደ ወገኖቹም ወደ አባቱም ርስት ይመለስ።
- 42
ከግብፅ ምድር ያወጣኋቸው ባሪያዎቼ ናቸውና እንደ ባሪያዎች አይሸጡ።
- 43
በጽኑ እጅ አትግዛው፥ ነገር ግን አምላክህን ፍራ።
- 44
ወንድ ባሪያና ሴት ባሪያ መግዛት ብትፈልግ ግን በዙሪያችሁ ካሉት ከእነርሱ ከአሕዛብ ወንድና ሴት ባሪያዎችን ግዙ።
- 45
ደግሞም በእናንተ መካከል ከሚቀመጡት መጻተኞች፥ በምድራችሁም ውስጥ ከወለዱአቸው በእናንተ መካከል ከሚቀመጡት ከዘራቸው ውስጥ ባሪያዎችን ግዙ፤ ርስትም ይሁኑላችሁ።
- 46
ከእናንተም በኋላ ልጆቻችሁ ይወርሱአቸው ዘንድ ተዉአቸው፤ ከእነርሱም ባሪያዎችን ለዘላለም ትወስዳላችሁ፤ ነገር ግን የእስራኤልን ልጆች ወንድሞቻችሁን በጽኑ እጅ አትግዙአቸው።
- 47
በአንተም ዘንድ የሚኖር መጻተኛ ወይም እንግዳ ሀብታም ቢሆን፥ ወንድምህም በእርሱ አጠገብ ቢደኸይ፥ ራሱንም ለመጻተኛው ወይም ለእንግዳው ወይም ለወገኖቹ ዘር ቢሸጥ፥
- 48
ከተሸጠ በኋላ መቤዠት ይችላል፤ ከወንድሞቹ አንዱ ይቤዠው፤
- 49
ወይም አጎቱ ወይም የአጎቱ ልጅ ይቤዠው፤ ወይም ከወገኑ ለእርሱ የቀረበ ዘመድ ይቤዠው፤ ወይም እርሱ እጁ ቢረጥብ ራሱን ይቤዠው።
- 50
ከገዛውም ሰው ጋር ከገዛበት ዓመት ጀምሮ እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ይቍጠር፤ የሽያጩም ብር እንደ ዓመታቱ ቍጥር ይሁን፤ እንደ ምንደኛውም ዘመን ከእርሱ ጋር ይሁን።
- 51
ብዙ ዓመታትም ቢቀሩ እንደ እነርሱ ቍጥር ከሽያጩ ብር የመቤዠቱን ዋጋ ይመልስ።
- 52
እስከ ኢዮቤልዩ ዓመት ድረስ ጥቂቶች ዓመታት ቢቀሩ ከእርሱ ጋር ይቈጥራል፤ እንደ ዓመታቱም መጠንየመቤዠቱን ዋጋ ይመልስ።
- 53
በየዓመቱ እንደ ምንደኛ ከእርሱ ጋር ይኑር፤ በፊትህ በጽኑ እጅ አይግዛው።
- 54
በዚህ ዘመን ሁሉ ግን ባይቤዥ በኢዮቤልዩ ዓመት እርሱ ከልጆቹ ጋር ይውጣ።
- 55
የእስራኤል ልጆች ለእኔ ባሪያዎች ናቸውና፤ ከግብፅ ምድር ያወጣኋቸው ባሪያዎቼ ናቸው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።