Job 40
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
እግዚአብሔርም መለሰ ኢዮብንም እንዲህ አለው።
- 2
በውኑ የሚከራከር ሰው ሁሉን ከሚችል አምላክ ጋር ይከራከራልን? ከእግዚአብሔር ጋር የሚዋቀስ እርሱ ይመልስለት።
- 3
ኢዮብም መለሰ እግዚአብሔርንም እንዲህ አለው።
- 4
እነሆ፥ እኔ ወራዳ ሰው ነኝ፤ የምመልስልህ ምንድር ነው? እጄን በአፌ ላይ እጭናለሁ።
- 5
አንድ ጊዜ ተናገርሁ፥ አልመልስምም፤ ሁለተኛ ጊዜም፥ ከእንግዲህ ወዲህ አልናገርም።
- 6
እግዚአብሔርም በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ ለኢዮብ መለሰ እንዲህም አለ።
- 7
እንግዲህ እንደ ወንድ ወገብህን ታጠቅ፤ እጠይቅሃለሁ፥ አንተም ተናገረኝ።
- 8
በውኑ ፍርዴን ታፈርሳለህን? አንተስ ጻድቅ ትሆን ዘንድ በእኔ ትፈርዳለህን?
- 9
እንደ እግዚአብሔር ክንድ ያለ ክንድ አለህን? ወይስ እንደ እርሱ ባለ ድምፅ ታንጐደጕዳለህን?
- 10
በታላቅነትና በልዕልና ተላበስ፤ በክብርና በግርማም ተጐናጸፍ።
- 11
የቍጣህን ፈሳሽ አፍስስ፤ ትዕቢተኛውንም ሁሉ ተመልክተህ አዋርደው።
- 12
ትዕቢተኛውንም ሁሉ ተመልከት፥ ዝቅ ዝቅም አድርገው፤ በደለኞችንም ወዲያውኑ እርገጣቸው።
- 13
በአፈር ውስጥ በአንድነት ሰውራቸው፤ በተሸሸገም ስፍራ ፊታቸውን ሸፍን።
- 14
በዚያን ጊዜም ቀኝ እጅህ ታድንህ ዘንድ እንድትችል እኔ ደግሞ እመሰክርልሃለሁ።
- 15
ከአንተ ጋር የሠራሁትን ጉማሬ፥ እስኪ፥ ተመልከት፤ እንደ በሬ ሣር ይበላል።
- 16
እነሆ፥ ብርታቱ በወገቡ ውስጥ ነው፤ ኃይሉም በሆዱ ጅማት ውስጥ ነው።
- 17
ጅራቱን እንደ ጥድ ዛፍ ያወዛውዛል፤ የወርቹ ጅማት የተጐነጐነ ነው።
- 18
አጥንቱ እንደ ናስ አገዳ ነው፤ አካላቱ እንደ ብረት ዘንጎች ናቸው።
- 19
እርሱ የእግዚአብሔር ፍጥረት አውራ ነው፤ ሠሪውም ሰይፉን ሰጠው።
- 20
የሜዳ እንስሶች ሁሉ የሚጫወቱበት ተራራ ምግብን ያበቅልለታል።
- 21
ጥላ ካለው ዛፍ በታች፥ በደንገልና በረግረግ ውስጥ ይተኛል።
- 22
ጥላ ያለው ዛፍ በጥላው ይሰውረዋል፤ የወንዝ አኻያ ዛፎች ይከብቡታል።
- 23
እነሆ፥ ወንዙ ቢጐርፍ አይደነግጥም፤ ዮርዳኖስም እስከ አፉ ድረስ ቢፈስስ እርሱ ይተማመናል።
- 24
ዓይኖቹ እያዩ ይያዛልን? አፍንጫውስ በወጥመድ ይበሳልን?