Job 31
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
ከዓይኔ ጋር ቃል ኪዳን ገባሁ፤ እንግዲህስ ቈንጆይቱን እንዴት እመለከታለሁ?
- 2
የእግዚአብሔር እድል ፈንታ ከላይ፥ ሁሉንም የሚችል አምላክ ርስት ከአርያም ምንድር ነው?
- 3
መዓትስ ለኃጢአተኛ፥ መለየትስ ለሚበድሉ አይደለምችን?
- 4
መንገዴን አያይምን? እርምጃዬንስ ሁሉ አይቈጥርምን?
- 5
- 6
በእውነተኛ ሚዛን ልመዘን፥ እግዚአብሔርም ቅንነቴን ይወቅ። በሐሰት ሄጄ እንደ ሆነ እግሬም ለሽንገላ ቸኵላ እንደ ሆነ፥
- 7
እርምጃዬ ከመንገድ ፈቀቅ ብሎ፥ ልቤም ዓይኔን ተከትሎ፥ ነውርም ከእጄ ጋር ተጣብቆ እንደ ሆነ፥
- 8
እኔ ልዝራ፥ ሌላ ሰውም ይብላው፤ የሚበቅለውም ሁሉ ይነቀል።
- 9
ልቤ ወደ ሌላይቱ ሴት ጐምጅቶ እንደ ሆነ፥ በባልንጀራዬም ደጅ አድብቼ እንደ ሆነ፥
- 10
ሚስቴ ለሌላ ሰው ትፍጭ፥ ሌሎችም በእርስዋ ላይ ይጐንበሱ።
- 11
ይህ ክፉ አበሳ፥ ፈራጆችም የሚቀጡበት በደል ነውና፤
- 12
ይህ እስከ ጥፋት ድረስ የሚበላ እሳት፥ ቡቃያዬንም ሁሉ የሚነቅል ነውና።
- 13
ወንድ ባሪያዬ ወይም ሴት ባሪያዬ ከእኔ ጋር በተምዋገቱ ጊዜ፥ ሙግታቸውን ንቄ እንደ ሆነ፥
- 14
እግዚአብሔር በተነሣ ጊዜ ምን አደርጋለሁ? በጐበኘኝ ጊዜ ምን እመልስለታለሁ?
- 15
እኔን በማኅፀን የፈጠረ እርሱንስ የፈጠረው አይደለምን? በማኅፀንስ ውስጥ የሠራን አንድ አይደለንምን?
- 16
ድሀውን ከልመናው ከልክዬ፥ የመበለቲቱን ዓይን አጨልሜ እንደ ሆነ፥
- 17
እንጀራዬን ለብቻዬ በልቼ እንደ ሆነ፥ ድሀ አደጉም ደግሞ ከእርሱ ሳይበላ ቀርቶ እንደ ሆነ፤
- 18
እርሱን ግን ከታናሽነቴ ጀምሬ እንደ አባቱ ከእኔ ጋር አሳድጌው ነበር፥ እርስዋንም ከእናቴ ማኅፀን ጀምሬ መራኋት፤
- 19
ራቁቱን የሆነው ሰው ሲጠፋ፥ ወይም ድሀ ያለ ልብስ ሲሆን አይቼ እንደ ሆነ፥
- 20
ጐንና ጐኑ ያልባረከችኝ፥ በበጎቼም ጠጕር ያልሞቀ እንደ ሆነ፤
- 21
በበሩ ረዳት ስላየሁ፥ በድሀ አደጉ ላይ እጄን አንሥቼ እንደ ሆነ፥
- 22
ትከሻዬ ከመሠረትዋ ትውደቅ፥ ክንዴም ከመገናኛዋ ትሰበር።
- 23
የእግዚአብሔር መዓት አስደንግጦኛልና፤ በክብሩም ፊት ምንም ለማድረግ አልቻልሁም።
- 24
ወርቅን ተስፋ አድርጌ፥ ጥሩውንም ወርቅ። በአንተ እታመናለሁ ብዬ እንደ ሆነ፤
- 25
ሀብቴ ስለ በዛ፥ እጄም ብዙ ስላገኘች ደስ ብሎኝ እንደ ሆነ፤
- 26
ፀሐይ ሲበራ ጨረቃ በክብር ስትሄድ አይቼ፥
- 27
ልቤ በስውር ተታልሎ፥ አፌም እጄን ስሞ እንደ ሆነ፤
- 28
ልዑል እግዚአብሔርን በካድሁ ነበርና ይህ ደግሞ ፈራጆች የሚቀጡበት በደል በሆነ ነበር።
- 29
በሚጠላኝ መጥፋት ደስ ብሎኝ ክፉ ነገርም ባገኘው ጊዜ ሐሤት አድርጌ እንደ ሆነ፤
- 30
ነገር ግን በመርገም ነፍሱን በመሻት አንደበቴን ኃጢአት ይሠራ ዘንድ አልሰጠሁም፤
- 31
በድንኳኔ የሚኖሩ ሰዎች። በከብቱ ሥጋ ያልጠገበ ማን ይገኛል? ብለው እንደ ሆነ፤
- 32
መጻተኛው ግን በሜዳ አያድርም ነበር፥ ደጄንም ለመንገደኛ እከፍት ነበር፤
- 33
በደሌንም በብብቴ በመሸሸግ ኃጢአቴን እንደ ሰው ሰውሬ እንደ ሆነ፤
- 34
ከሕዝብ ብዛት ፈርቼ፥ የዘመዶቼም ንቀት አስደንግጦኝ፥ ዝም ብዬ ከደጅ ያልወጣሁ እንደ ሆነ፤
- 35
የሚያዳምጠኝ ምነው በኖረልኝ! እነሆ የእጄ ምልክት ሁሉን የሚችል አምላክ ይመልስልኝ፤ ከባላጋራዬ የተጻፈው የክስ ጽሑፍ ምነው በተገኘልኝ!
- 36
በትከሻዬ ላይ እሸከመው፥ አክሊልም አድርጌ በራሴ አስረው ነበር፤
- 37
የእርምጃዬን ቍጥር አስታውቀው፥ እንደ አለቃም ሆኜ አቀርብለት ነበር።
- 38
እርሻዬ በእኔ ላይ ጮኻ እንደ ሆነ፥ ትልሞችዋም በአንድ ላይ አልቅሰው እንደ ሆነ፤
- 39
ፍሬዋን ያለ ዋጋ በልቼ፥ የባለቤቶችንም ነፍስ አሳዝኜ እንደ ሆነ፥
- 40
በስንዴ ፋንታ አሜከላ፥ በገብስም ፋንታ ኵርንችት ይውጣብኝ። የኢዮብ ቃል ተፈጸመ።