Job 22
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
ቴማናዊውም ኤልፋዝ መለሰ እንዲህም አለ።
- 2
በውኑ ሰው እግዚአብሔርን ይጠቅመዋልን? በእውነት ጥበበኛ ሰው ራሱን ይጠቅማል።
- 3
ጻድቅ መሆንህስ ሁሉን የሚችለውን አምላክ ደስ ያሰኘዋልን? መንገድህን ማቅናትህስ ይጠቅመዋልን?
- 4
እርሱንስ ስለ ፈራህ ይዘልፍሃልን? ወደ ፍርድስ ከአንተ ጋር ይገባልን?
- 5
ክፋትህስ የበዛ አይደለምን? ለኃጢአትህም ፍጻሜ የላትም።
- 6
የወንድሞችህን መያዣ በከንቱ ወስደሃል፥ የእርዘኞቹንም ልብስ ዘርፈሃል።
- 7
ለደካማ ውኃ አላጠጣህም፥ ለራብተኛም እንጀራን ከልክለሃል።
- 8
በክንድ የበረታ ምድርን ገዛ፤ ከበርቴውም ሰው ተቀመጠባት።
- 9
መበለቲቱን አንዳች አልባ ሰድደሃታል፤ የድሀ አደጎችም ክንድ ተሰብሮአል።
- 10
ስለዚህ አሽክላ ከብቦሃል፥ ድንገተኛ ፍርሃትም አናውጦሃል።
- 11
እንዳታይ ብርሃን ጨለማ ሆነችብህ፥ የውኆችም ብዛት አሰጠመህ።
- 12
እግዚአብሔር በሰማያት ከፍ ከፍ አይልምን? ከዋክብትም እንዴት ከፍ ከፍ እንዳሉ ተመልከት።
- 13
አንተም። እግዚአብሔር ምን ያውቃል? በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ሆኖ ሊፈርድ ይችላልን?
- 14
እንዳያይ የጠቈረ ደመና ጋርዶታል፤ በሰማይ ክበብ ላይ ይራመዳል ብለሃል።
- 15
በውኑ ኃጢአተኞች ሰዎች የረገጡአትን የዱሮይቱን መንገድ ትጠብቃለህን?
- 16
ጊዜያቸው ሳይደርስ ተነጠቁ፤ መሠረታቸውም እንደ ፈሳሽ ውኃ ፈሰሰ።
- 17
እግዚአብሔርንም። ከእኛ ዘንድ ራቅ፤ ሁሉንም የሚችል አምላክ ምን ሊያደርግልን ይችላል? አሉት።
- 18
ነገር ግን ቤታቸውን በመልካም ነገር ሞላ፤ የኃጥአን ምክር ከእኔ ዘንድ የራቀች ናት።
- 19
ጻድቃን ያዩታል፥ ደስም ይላቸዋል፤ ንጹሐንም በንቀት ይስቁባቸዋል።
- 20
በእውነት ሀብታቸው ጠፋ፥ የቀረውንም እሳት በላች።
- 21
አሁንም ከእርሱ ጋር ተስማማ፥ ሰላምም ይኑርህ፤ በዚያም በጎነት ታገኛለህ።
- 22
ከአፉም ሕጉን ተቀበል፥ በልብህም ቃሉን አኑር፤
- 23
ሁሉን ወደሚችል አምላክ ብትመለስ፥ ብትዋረድም፥ ኃጢአትንም ከድንኳንህ ብታርቅ፥
- 24
የወርቅን ዕቃ በአፈር ውስጥ፥ የኦፊርንም ወርቅ በጅረት ድንጋይ መካከል ብትጥል፥
- 25
ሁሉን የሚችል አምላክ ወርቅና የሚብለጨለጭ ብር ይሆንልሃል።
- 26
የዚያን ጊዜ ሁሉን በሚችል አምላክ ደስ ይልሃል፥ ፊትህንም ወደ እግዚአብሔር ታነሣለህ።
- 27
ወደ እርሱም ትጸልያለህ፥ እርሱም ይሰማሃል፤ ስእለትህንም ትሰጣለህ።
- 28
ነገርንም ትመክራለህ፥ እርሱም ይሳካልሃል፤ ብርሃንም በመንገድህ ላይ ይበራል።
- 29
ቢያዋርዱህ አንተ ከፍ ከፍ ትላለህ፤ ትሑቱንም ሰው ያድነዋል።
- 30
ንጹሑን ሰው ያድነዋል፤ በእጅህም ንጽሕና ትድናለህ።