Job 20
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
ናዕማታዊውም ሶፋር መለሰ እንዲህም አለ።
- 2
ስለዚህ በውስጤ ስላለው ችኰላ አሳቤ ትመልስልኛለች።
- 3
የሚያሳፍረኝንም ተግሣጽ ሰምቻለሁ፥ የማስተዋሌም መንፈስ ይመልስልኛል።
- 4
ሰው በምድር ላይ ከተቀመጠ፥ ከዱሮ ዘመን ጀምሮ፥
- 5
የኃጢአተኛ ፉከራ አጭር መሆኑን የዝንጉዎችም ደስታ ቅጽበት መሆኑን አታውቁምን?
- 6
ከፍታው ወደ ሰማይ ቢወጣ፥ ራሱም እስከ ደመና ቢደርስ፥
- 7
እንደ ፋንድያ ለዘላለም ይጠፋል፤ ያዩትም። ወዴት ነው? ይላሉ።
- 8
እንደ ሕልም ይበርራል፥ እርሱም አይገኝም፤ እንደ ሌሊትም ራእይ ይሰደዳል።
- 9
ያየችውም ዓይን ዳግመኛ አታየውም፤ ስፍራውም ከእንግዲህ ወዲህ አይመለከተውም።
- 10
ልጆቹ ድሆቹን ያቈላምጣሉ፤ እጁ ሀብቱን ይመልሳል።
- 11
አጥንቶቹ ብላቴንነቱን ሞልተዋል፤ ነገር ግን ከእርሱ ጋር በመሬት ውስጥ ይተኛል።
- 12
ክፋት በአፉ ውስጥ ቢጣፍጥ፥ ከምላሱም በታች ቢሰውረው፥
- 13
ቢጠብቀውም ባይተወውም፥ በጕሮሮውም ቢይዘው፥
- 14
መብሉ በአንጀቱ ውስጥ ይገላበጣል፤ እንደ እፉኝትም ሐሞት በውስጡ ይሆናል።
- 15
የዋጠውን ሀብት ይተፋዋል፤ እግዚአብሔርም ከሆዱ ውስጥ ያወጣዋል።
- 16
የእፉኝትን መርዝ ይጠባል፤ የእባብም ምላስ ይገድለዋል።
- 17
የማሩንና የቅቤውን ፈሳሽ ወንዞቹንም አይመለከትም።
- 18
የድካሙን ፍሬ ሳይውጠው ይመልሰዋል፤ እንደ ንግዱም ትርፍ አይደሰትም።
- 19
ድሀውን አስጨንቆአል፥ ትቶታልም፤ ያልሠራውንም ቤት በዝብዞአል።
- 20
ሆዱ ዕረፍትን አላወቀምና የወደደው ነገር አላዳነውም።
- 21
እርሱ ከበላ በኋላ ምንም አልተረፈም፤ ስለዚህ በረከቱ አይከናወንለትም።
- 22
በጠገበ ጊዜ ይጨነቃል፤ የችግረኞችም ሁሉ እጅ ታገኘዋለች።
- 23
ሆዱን ሳያጠግብ እግዚአብሔር የቍጣውን ትኵሳት ይሰድድበታል፥ ሲበላም ያዘንብበታል።
- 24
ከብረት መሣርያም ይሸሻል፥ የናስም ቀስት ይወጋዋል።
- 25
እርሱም ይመዝዘዋል፥ ከሥጋውም ይወጣል፤ ከሐሞቱም ብልጭ ብሎ ይሠርጻል፤ ፍርሃትም ይወድቅበታል።
- 26
ጨለማ ሁሉ ስለ ከበረው ዕቃ ተዘጋጅቶአል፤ በሰው አፍ እፍ የማትባል እሳት ትበላዋለች፤ በድንኳኑ ውስጥ የቀረው ይጨነቅባታል።
- 27
ሰማይ ኃጢአቱን ይገልጥበታል፥ ምድርም ትነሣበታለች።
- 28
የቤቱም ባለጠግነት ይሄዳል፤ በቍጣው ቀን እንደ ፈሳሽ ውኃ ያልፋል።
- 29
ከእግዚአብሔር ዘንድ የበደለኛ ሰው እድል ፈንታ፥ ከእግዚአብሔርም የተመደበ ርስቱ ይህ ነው።