Job 16
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
ኢዮብም መለሰ እንዲህም አለ።
- 2
እንደዚህ ያለ ዓይነት ነገር እጅግ ሰማሁ፤ እናንተ ሁላችሁ የምታደክሙ አጽናኞች ናችሁ።
- 3
በውኑ ከንቱ ቃል ይፈጸማልን? ወይስ ትመልስ ዘንድ ያነሣሣህ ምንድር ነው?
- 4
እኔ ደግሞ እንደ እናንተ እናገር ዘንድ ይቻለኝ ነበር፤ ነፍሳችሁ በነፍሴ ፋንታ ቢሆን ኖሮ፥ እኔ በእናንተ ላይ ቃል ማሳካት፥ ራሴንም በእናንተ ላይ መነቅነቅ በተቻለኝ ነበር።
- 5
በአፌም ነገር ባበረታኋችሁ ነበር፤ የከንፈሬን ማጽናናት ባልከለከልሁም ነበር።
- 6
እኔ ብናገር ሕማሜ አይቀነስም፤ ዝምም ብል ከእኔ አይወገድም።
- 7
አሁን ግን አድክሞኛል፤ ወገኔንም ሁሉ አፍርሰሃል።
- 8
መጨማተሬ ይመሰክርብኛል፤ ክሳቴም ተነሥቶብኛል፤ በፊቴም ይመሰክርብኛል።
- 9
በቍጣው ቀደደኝ፥ እርሱም ጠላኝ፤ ጥርሶቹንም አፋጨብኝ፤ ጠላቴ ዓይኑን አፈጠጠብኝ፤
- 10
እነርሱም አፋቸውን ከፈቱብኝ፤ እያላገጡ ጕንጬን ጠፈጠፉኝ፤ በአንድነትም ተሰበሰቡብኝ።
- 11
እግዚአብሔር ለጠማማ ሰው አሳልፎ ሰጠኝ፥ በክፉዎችም እጅ ጣለኝ።
- 12
ተዘልዬ ተቀምጬ ነበር፥ እርሱም ሰበረኝ፤ አንገቴንም ይዞ ቀጠቀጠኝ፤ እንደ ዓላማ አድርጎ አቆመኝ።
- 13
ቀስተኞቹ ከበቡኝ፤ ኵላሊቴንም ቈራረጠ፥ እርሱም አልራራም፤ ሐሞቴን በምድር ላይ አፈሰሰ።
- 14
በቍስል ላይ ቍስል ጨመረብኝ፤ እንደ ኃያል እየሠገገ ይሮጥብኛል።
- 15
በቁርበቴ ላይ ማቅ ሰፋሁ፥ ቀንዴንም በመሬት ላይ አኖርሁ።
- 16
ፊቴ ከልቅሶ የተነሣ ቀላ፤ የሞት ጥላ በዓይኖቼ ቆብ ላይ አለ፤
- 17
ነገር ግን በእጄ ዓመፅ የለም፤ ጸሎቴም ንጹሕ ነው።
- 18
ምድር ሆይ፥ ደሜን አትክደኚ፥ ለጩኸቴም ማረፊያ አይሁን።
- 19
አሁንም፥ እነሆ፥ ምስክሬ በሰማይ አለ፥ የሚመሰክርልኝም በአርያም ነው።
- 20
ጸሎቴ ወደ እግዚአብሔር ይድረስ፥ ዓይኔም በፊቱ እንባ ታፍስስ።
- 21
የሰው ልጅ ከባልንጀራው ጋር እንደሚምዋገት፥ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ለመምዋገት ምነው በቻለ!
- 22
ጥቂቶች ዓመታት ካለፉ በኋላ እኔ ወደማልመለስበት መንገድ እሄዳለሁ።