Jeremiah 8
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
በዚያን ዘመን፥ ይላል እግዚአብሔር፥ የይሁዳን ነገሥታት አጥንትና የመኳንንቶቹን አጥንት፥ የካህናቱን አጥንትና የነቢያቱን አጥንት፥ የኢየሩሳሌምንም ሰዎች አጥንት ከመቃብራቸው ያወጣሉ።
- 2
በወደዱአቸውና ባመለኩአቸው፥ በተከተሉአቸውና በፈለጉአቸው፥ በሰገዱላቸውም በፀሐይና በጨረቃ በሰማይም ሠራዊት ሁሉ ፊት ይዘረጉአቸዋል፤ አያከማቹአቸውም አይቀብሩአቸውምም፥ በምድርም ፊት ላይ እንደ ጕድፍ ይሆናሉ።
- 3
እኔም ባሳደድኋቸው ስፍራ ሁሉ የቀሩ፥ ከዚህች ክፉ ወገን የተረፉ ቅሬታዎች ሁሉ፥ ከሕይወት ይልቅ ሞትን ይመርጣሉ።
- 4
እንዲህም ትላቸዋለሁ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የወደቁ አይነሡምን? የሳተስ አይመለስምን?
- 5
እንግዲህ ይህ የኢየሩሳሌም ሕዝብ ዘወትር ስለ ምን ወደ ኋላው ይመለሳል? ተንኰልን ይዞአል ሊመለስም እንቢ ብሎአል።
- 6
አደመጥሁ ሰማሁም፤ ቅንን ነገር አልተናገሩም፤ ማናቸውንም። ምን አድርጌአለሁ? ብሎ ከክፋቱ ንስሐ የገባ የለም፤ ወደ ሰልፍም እንደሚሮጥ ፈረስ እያንዳንዱ በየመንገዱ ይሄዳል።
- 7
ሽመላ በሰማይ ጊዜዋን አውቃለች፤ ዋኖስና ጨረባ ዋልያም የመምጣታቸውን ጊዜ ይጠብቃሉ፤ ሕዝቤ ግን የእግዚአብሔርን ፍርድ አላወቁም።
- 8
እናንተስ። ጥበበኞች ነን የእግዚአብሔርም ሕግ ከእኛ ጋር ነው እንዴት ትላላችሁ? እነሆ፥ የጸሐፊ ብርዕ ሐሰተኛ ነው በሐሰትም አድርጎአል።
- 9
ጥበበኞች አፍረዋል ደንግጠውማል ተማርከውማል፤ እነሆ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ጥለዋል፤ ምን ዓይነት ጥበብ አላቸው?
- 10
ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ስስትን ያስባሉና፥ ከነቢዩም ጀምሮ እስከ ካህኑ ድረስ ሁሉ በተንኰል ያደርጋሉና ስለዚህ ሚስቶቻቸውን ለሌሎች፥ እርሻቸውንም ለሚወርሱባቸው እሰጣለሁ።
- 11
የሕዝቤንም ሴት ልጅ ስብራት በጥቂቱ ይፈውሳሉ፤ ሰላም ሳይሆን። ስለም ሰላም ይላሉ።
- 12
አስጸያፊ ነገርን ስለ ሠሩ አፍረዋልን? ምንም አላፈሩም፥ እፍረትንም አላወቁም፤ ስለዚህ ከሚወድቁ ጋር ይወድቃሉ፤ በጐበኘኋቸው ጊዜ ይዋረዳሉ፥ ይላል እግዚአብሔር
- 13
ፈጽሜ አጠፋችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ በወይን ላይ ፍሬ፥ በበለስ ዛፍ ላይ በለስ አይሆንም፥ ቅጠልም ይረግፋል፤ የሚያልፉባቸውንም ሰጠኋቸው።
- 14
ዝም ብለን ለም እንቀመጣለን? እግዚአብሔርን ስለ በደልን አምላካችን እግዚአብሔር አጥፍቶናልና፥ የሐሞትንም ውኃ አጠጥቶናልና ተሰብስባችሁ ወደ ተመሸጉ ከተሞች እንግባ በዚያም እንጥፋ።
- 15
ሰላምን በተስፋ ተጠባበቅን፥ መልካምም አልተገኘም፤ መጠገንን በተስፋ ተጠባበቅን፥ እነሆም፥ ድንጋጤ ሆነ።
- 16
የፈረሰኞቹ ድምጽ ከዳን ተሰማ፤ ከአርበኞች ፈረሶች ማሽካካት የተነሣ ምድር ሁሉ ተንቀጠቀጠች፤ መጡም ምድሪቱንና በእርስዋም ያለውን ሁሉ፥ ከተማይቱንና የተቀመጡባትንም በሉ።
- 17
እነሆ፥ አስማት የማይከለክላቸውን እባቦችንና እፉኝቶችን እሰድድባችኋለሁ፤ እነርሱም ይነድፉአችኋል።
- 18
ኅዘኔ የማይጽናና ነው፥ ልቤም በውስጤ ደክሞአል።
- 19
እነሆ። እግዚአብሔር በጽዮን የለምን? ወይስ ንጉሥዋ በእርስዋ ዘንድ የለምን? የሚል የወገኔ ሴት ልጅ ጩኸት ድምፅ ከሩቅ አገር ተሰማ። በተቀረጹ ምስሎቻቸውና በባዕድ ከንቱነትስ ያስቈጡኝ ስለ ምንድር ነው?
- 20
መከሩ አልፎአል፥ በጋው ሄዶአል፥ እኛም አልዳንነም።
- 21
በሕዝቤ ሴት ልጅ ስብራት እኔ ተሰብሬአለሁ ጠKWreማለሁ፤ አድናቆትም ይዞኛል።
- 22
በገለዓድ የሚቀባ መድኃኒት የለምን? ወይስ በዚያ ሐኪም የለምን? የወገኔ ሴት ልጅ ፈውስ ስለ ምን አልሆነም?