Jeremiah 6
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
እናንተ የብንያም ልጆች፥ ክፉ ነገር ታላቅም ጥፋት ከሰሜን ይጐበኛልና ከኢየሩሳሌም ውስጥ ሽሹ፥ በቴቁሔ መለከቱን ንፉ፥ በቤትሐካሪም ላይ ምልክት አንሡ።
- 2
የተዋበችውንና የተሰባቀለችውን የጽዮንን ልጅ አጐሰቍላለሁ።
- 3
እረኞችና መንጐቻቸው ወደ እርስዋ ይመጣሉ፥ በዙሪያዋም ድንኳኖቻቸውን ይተክሉባታል፥ እያንዳንዱም በስፍራው መንጋውን ያሰማራል።
- 4
በእርስዋ ላይ ሰልፍ አዘጋጁ ተነሡ፥ በቀትርም እንውጣ። ቀኑ መሽቶአልና፥ የማታውም ጥላ ረዝሞአልና ወዮልን።
- 5
ተነሡ በሌሊትም እንውጣ፥ አዳራሾችዋንም እናፍርስ።
- 6
የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። ዛፎችዋን ቍረጡ፥ በኢየሩሳሌምም ላይ አፈርን ደልድሉ፤ ይህች ከተማ የምትቀሠፍ ናት፤ መካከልዋ ሁሉ ግፍ ብቻ ነው።
- 7
በጕድጓድ ውኃ እንደሚፈልቅ፥ እንዲሁ ክፋትዋ ከእርስዋ ዘንድ ይፈልቃል፤ ግፍና ቅሚያ በእርስዋ ዘንድ ይሰማል፥ ደዌና ቍስልም ሁልጊዜ በፊቴ አለ።
- 8
ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ነፍሴ ከአንቺ እንዳትለይ፥ አንቺንም ባድማና ወና እንዳላደርግሽ፥ ተግሣጽን ተቀበዪ።
- 9
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሰው ወይኑን እንደሚቃርም፥ እንዲሁ ከእስራኤል የቀሩትን ፈጽሞ ይቃርሙአቸዋል፤ እጅህንም እንደ ለቃሚ ወደ እንቅብ ዘርጋ።
- 10
ይሰሙኝስ ዘንድ ለማን እናገራለሁ? ለማንስ አስጠነቅቃለሁ? እነሆ፥ ጆሮአቸው ያልተገረዘች ናት ለመስማትም አይችሉም፤ እነሆ፥ የእግዚአብሔር ቃል ለስድብ ሆኖባቸዋል፥ ደስም አያሰኛቸውም።
- 11
ስለዚህ በእግዚአብሔር ቍጣ ተሞልቻለሁ፤ ከመታገሥ ደክሜአለሁ፤ በሜዳ በሕፃናት ላይ በጕልማሶችም ጉባዔ ላይ በአንድነት አፍስሰው፤ ባል ከሚስቱ ጋር ሽማግሌውም ከጎበዙ ጋር ይያያዛልና።
- 12
እጄን በምድር በሚኖሩ ላይ እዘረጋለሁና ቤቶቻቸው እርሻዎቻቸውም ሴቶቻቸውም በአንድነት ለሌሎች ይሆናሉ፥ ይላል እግዚአብሔር።
- 13
ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ስስትን ያስባሉና፥ ከነቢዩም ጀምሮ እስከ ካህኑ ድረስ ሁሉ በተንኰል ያደርጋሉና።
- 14
የሕዝቤንም ስብራት በጥቂቱ ይፈውሳሉ፤ ሰላም ሳይሆን። ሰላም ሰላም ይላሉ።
- 15
ርኩስን ነገር ስለ ሠሩ አፍረዋልን? ምንም አላፈሩም፥ እፍረትንም አላወቁም፤ ስለዚህ ከሚወድቁ ጋር ይወድቃሉ፤ በጐበኘኋቸው ጊዜ ይዋረዳሉ፥ ይላል እግዚአብሔር።
- 16
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በመንገድ ላይ ቁሙ ተመልከቱም፥ የቀደመችውንም መንገድ ጠይቁ፤ መልካሚቱ መንገድ ወዴት እንደ ሆነች እወቁ፥ በእርስዋም ላይ ሂዱ፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ እነርሱ ግን። አንሄድባትም አሉ።
- 17
እኔም። የመለከቱን ድምፅ አድምጡ ብዬ ጠባቆችን ሾምሁባችሁ፤ እነርሱ ግን። አናደምጥም አሉ።
- 18
አሕዛብ ሆይ፥ ስለዚህ ስሙ፤ ማኅበር ሆይ፥ እነዚያ የሚያገኛቸውን እወቁ።
- 19
ምድር ሆይ፥ ስሚ፤ እነሆ፥ ቃሌን ስላልሰሙ ሕጌንም ስለ ጣሉ በዚህ ሕዝብ ላይ የአሳባቸውን ፍሬ ክፉን ነገር አመጣባቸዋለሁ።
- 20
ስለ ምንስ ከሳባ ዕጣንን፥ ከሩቅም አገር ቀረፋን ታቀርቡልኛላችሁ? የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁን አልቀበለውም ሌላ መሥዋዕታችሁም ደስ አያሰኘኝም።
- 21
ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ከዚህ ሕዝብ ፊት ዕንቅፋቶችን አደርጋለሁ፤ አባቶችና ልጆች በአንድነት ይሰናከሉባቸዋል፥ ጎረቤትና ባልንጀራም ይጠፋሉ።
- 22
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ሕዝብ ከሰሜን አገር ይመጣል፥ ታላቅ ሕዝብም ከምድር ዳርቻ ይነሣል።
- 23
ቀስትንና ጦርን ይይዛሉ፤ ጨካኞች ናቸው፥ ምሕረትንም አያደርጉም፤ ድምፃቸው እንደ ባሕር ይተምማል፥ በፈረሶችም ላይ ይቀመጣሉ፤ የጽዮን ሴት ልጅ ሆይ፥ ለሰልፍ እንደ ተዘጋጀ ሰው እያንዳንዳቸው በአንቺ ላይ ተሰለፉ።
- 24
ወሬውን ሰምተናል፥ እጃችን ደክማለች፤ ምጥ ወላድን ሴት እንደሚይዛት ጭንቀት ይዞናል።
- 25
የጠላት ሰይፍና ድንጋጤ ከብበዋችኋልና ወደ ሜዳ አትውጡ በምንገድም ላይ አትሂዱ።
- 26
የሕዝቤ ልጅ ሆይ፥ ማቅ ልበሺ በአመድም ውስጥ ተንከባለዪ፤ አጥፊ በላያችን በድንገት ይመጣብናልና ለአንድያ ልጅ እንደሚደረግ ልቅሶ፥ መራራ ልቅሶ አልቅሺ።
- 27
መንገዳቸውን እንድታውቅና እንድትፈትን በሕዝቤ መካከል ፈታኝ አድርጌሃለሁ።
- 28
እነርሱ ሁሉ እጅግ ዓመፀኞች ናቸው፤ በጠማማነት ይሄዳሉ፤ ናስና ብረት ናቸው፤ ሁሉ ርኵሰትን ያደርጋሉ።
- 29
ወናፍ አናፋ እርሳሱም በእሳት ቀለጠ፤ አንጥረኛውም መልሶ በከንቱ ያቀልጠዋል፤ ኃጢአተኞች አልተወገዱም።
- 30
እግዚአብሔር ጥሎአቸዋልና የተጣለ ብር ብለው ይጠሩአቸዋል።