Jeremiah 30
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው።
- 2
የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የነገርሁህን ቃል ሁሉ በመጽሐፍ ጻፍ።
- 3
እነሆ፥ የሕዝቤን የእስራኤልንና የይሁዳን ምርኮ የምመልስባት ዘመን ይመጣልና፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ለአባቶቻቸውም ወደ ሰጠኋት ምድር እመልሳቸዋለሁ፥ እነርሱም ይገዙአታል።
- 4
እግዚአብሔር ስለ እስራኤልና ስለ ይሁዳ የተናገረው ቃል ይህ ነው።
- 5
እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። የሚያስፈራ ድምፅ ሰምተናል፤ የፍርሃት ነው እንጂ የሰላም አይደለም።
- 6
ጠይቁ፥ ወንድ ይወልድ እንደ ሆነ ተመልከቱ፤ ስለ ምን ሰው ሁሉ እንደ ወላድ እጁን በወገቡ ላይ አድርጎ ፊቱም ሁሉ ወደ ጥቁረት ተለውጦ አየሁ?
- 7
ወዮ! ያ ቀን ታላቅ ነውና፥ እርሱንም የሚመስል የለምና፤ ያ የያዕቆብ መከራ ዘመን ነው፥ ነገር ግን ከእርሱ ይድናል።
- 8
በዚያ ቀን እንዲህ ይሆናል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ቀንበርን ከአንገትህ እሰብራለሁ፥ እስራትህንም እበጥሳለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲህም ለሌላ አትገዛም፤
- 9
ለአምላካቸው ለእግዚአብሔርም ለማስነሣላቸው ለንጉሣቸው ለዳዊትም ይገዛሉ እንጂ ሌሎች አሕዛብ እንደ ገና አይገዙአቸውም።
- 10
እነሆ፥ አንተን ከሩቅ ዘርህንም ከምርኮ አገር አድናለሁና ባሪያዬ ያዕቆብ ሆይ፥ አትፍራ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ አንተም እስራኤል ሆይ፥ አትደንግጥ፤ ያዕቆብም ይመለሳል ያርፍማል ተዘልሎም ይቀመጣል፤ ማንም አያስፈራውም።
- 11
አድንህ ዘንድ ከአንተ ጋር ነኝና፥ ይላል እግዚአብሔር፤ አንተንም የበተንሁባቸውን አሕዛብን ሁሉ ፈጽሜ አጠፋለሁ፥ አንተን ግን ፈጽሜ አላጠፋህም፤ በመጠን እቀጣሃለሁ፥ ያለ ቅጣትም ከቶ አልተውህም።
- 12
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ስብራትህ የማይፈወስ ቍስልህም ክፉ ነው።
- 13
ትጠገን ዘንድ ክርክርህን የሚፈርድልህ የለም፥ ቍስልህንም የሚፈውስ መድኃኒት የለህም።
- 14
ውሽሞችህ ሁሉ ረስተውሃል አይፈልጉህምም፤ በደልህ ታላቅ ስለሆነ ኃጢአትህም ስለ በዛ፥ በጠላት ማቍሰልና በጨካኝ ቅጣት አቍስዬሃለሁና።
- 15
ሕመምህ የማይፈወስ ሆኖአልና ስለ ስብራትህ ለምን ትጮኻለህ? በደልህ ታላቅ ስለሆነ ኃጢአትህም ስለ በዛ፥ ይህን አድርጌብሃለሁ።
- 16
ስለዚህ የሚውጡህ ሁሉ ይዋጣሉ፥ ጠላቶችህም ሁላቸው ይማረካሉ፤ የዘረፉህም ይዘረፋሉ፥ የበዘበዙህንም ሁሉ ለመበዝበዝ አሳልፌ እሰጣለሁ።
- 17
እኔ ጤናህን እመልስልሃለሁ ቍስልህንም እፈውሳለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ማንም የማይሻት፥ የተጣለች ጽዮን ብለው ጠርተውሻልና።
- 18
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ የያዕቆብን ድንኳን ምርኮ እመልሳለሁ፥ ለማደሪያውም እራራለሁ፤ ከተማይቱም በጉብታዋ ላይ ትሠራለች፥ አዳራሹም እንደ ዱሮው የሰው መኖሪያ ይሆናል።
- 19
ከእርሱም ዘንድ የምስጋናና የዘፋኞች ድምፅ ይወጣል፤ እኔም አበዛቸዋለሁ አያንሱምም፥ እኔም አከብራቸዋለሁ ታናሽም አይሆኑም።
- 20
ልጆቻቸውም እንደ ቀድሞ ይሆናሉ፥ ማኅበራቸውም በፊቴ ጸንቶ ይኖራል፤ የሚያስጨንቋቸውንም ሁሉ እቀጣለሁ።
- 21
አለቃቸው ከእነርሱ ውስጥ ይሆናል፥ ገዥአቸውም ከመካከላቸው ይወጣል፤ እኔ አቀርበዋለሁ እርሱም ይቀርባል፤ ይህስ ባይሆን ወደ እኔ ለመቅረብ የሚደፍር ማን ነው? ይላል እግዚአብሔር።
- 22
እናንተም ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ።
- 23
እነሆ፥ የእግዚአብሔር ዐውሎ ነፋስ፥ እርሱም ቍጣው፥ የሚያገለባብጥ ዐውሎ ነፋስ ወጥቶአል፤ የዓመፀኞችንም ራስ ይገለባብጣል።
- 24
የእግዚአብሔር ጽኑ ቍጣ የልቡን አሳብ ሠርቶ እስኪፈጽም ድረስ አይመለስም በኋለኛው ዘመን ታስተውሉታላችሁ።