Jeremiah 28
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
በዚያም ዓመት በይሁዳ ንጉሥ በሴዴቅያስ መንግሥት መጀመሪያ በአራተኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ነቢዩ የገባዖን ሰው የዓዙር ልጅ ሐናንያ በእግዚአብሔር ቤት በካህናትና በሕዝብ ሁሉ ፊት እንዲህ ብሎ ተናገረኝ።
- 2
የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ይናገራል። የባቢሎንን ንጉሥ ቀንበር ሰብሬአለሁ።
- 3
የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ከዚህች ስፍራ ወደ ባቢሎን የወሰዳትን የእግዚአብሔርን ቤት ዕቃ ሁሉ በሁለት ዓመት ውስጥ ወደዚህች ስፍራ እመልሳታለሁ፤
- 4
ወደ ባቢሎንም የሄዱትን የይሁዳን ንጉሥ የኢዮአቄምን ልጅ ኢኮንያንንና የይሁዳን ምርኮ ሁሉ ወደዚህች ስፍራ እመልሳቸዋለሁ፤ የባቢሎንን ንጉሥ ቀንበር እሰብራለሁና።
- 5
ነቢዩ ኤርምያስም በካህናቱና በእግዚአብሔር ቤት በቆሙት ሕዝብ ሁሉ ፊት ለነቢዩ ለሐናንያ ተናገረ።
- 6
ነቢዩም ኤርምያስ እንዲህ አለ። አሜን፥ እግዚአብሔር እንዲህ ያድርግ፤ የእግዚአብሔርን ቤት ዕቃ ምርኮውንም ሁሉ ከባቢሎን ወደዚህ ስፍራ በመመለስ እግዚአብሔር የተናገርኸውን ትንቢት ይፈጽም።
- 7
ነገር ግን በጆሮህና በሕዝብ ሁሉ ጆሮ የምናገረውን ይህን ቃል ስማ፤
- 8
ከጥንት ከእኔና ከአንተ በፊት የነበሩ ነቢያት በብዙ አገርና በታላላቅ መንግሥታት ላይ ስለ ሰልፍና ስለ ክፉ ነገር ስለ ቸነፈርም ትንቢት ተናገሩ።
- 9
ስለ ሰላም የተናገረ ነቢይ፥ የነቢዩ ቃል በሆነ ጊዜ፥ እግዚአብሔር በእውነት የሰደደው ነቢይ እንደ ሆነ ይታወቃል።
- 10
ነቢዩም ሐናንያ ቀንበሩን ከነቢዩ ከኤርምያስ አንገት ወስዶ ሰበረው።
- 11
ሐናንያም በሕዝብ ሁሉ ፊት። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እንዲሁ በሁለት ዓመት ውስጥ የባቢሎንን ንጉሥ የናቡከደነፆርን ቀንበር ከአሕዛብ ሁሉ አንገት እሰብራለሁ አለ። ነቢዩም ኤርምያስ መንገዱን ሄደ።
- 12
ነቢዩም ሐናንያ ቀንበሩን ከነቢዩ ከኤርምያስ አንገት ከሰበረ በኋላ፥ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ።
- 13
ሂድ፥ ለሐናንያ እንዲህ ብለህ ንገረው። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። አንተ የእንጨትን ቀንበር ሰብረሃል፥ እኔ ግን በእርሱ ፋንታ የብረትን ቀንበር እሠራለሁ።
- 14
የእስራኤልም አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር ይገዙለት ዘንድ የብረትን ቀንበር በእነዚህ አሕዛብ ሁሉ አንገት ላይ አድርጌአለሁ፤ እነርሱም ይገዙለታል፥ የምድረ በዳ አራዊት ደግሞ ሰጥቼዋለሁ።
- 15
ነቢዩም ኤርምያስ ነቢዩን ሐናንያን። ሐናንያ ሆይ፥ ስማ፤ ይህ ሕዝብ በሐሰት እንዲታመን አድርገሃል እንጂ እግዚአብሔር አልላከህም።
- 16
ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ከምድር ላይ እሰድድሃለሁ፤ በእግዚአብሔር ላይ ዓመፅን ተናግረሃልና በዚህ ዓመት ትሞታለህ አለው።
- 17
ነቢዩም ሐናንያ በዚያው ዓመት በሰባተኛው ወር ሞተ።