Jeremiah 23
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
የማሰማርያዬን በጎች ለሚያጠፉና ለሚበትኑ እረኞች ወዮላቸው! ይላል እግዚአብሔር።
- 2
ስለዚህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሕዝቤን ስለሚጠብቁ እረኞች እንዲህ ይላል። በጎቼን በትናችኋል አባርራችኋቸውማል አልጐበኛችኋቸውምም፤ እነሆ፥ የሥራችሁን ክፋት እጐበኝባችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
- 3
የመንጋዬም ቅሬታ ካባረርኋቸው ምድር ሁሉ ወደ በረታቸው ሰብሰቤ እመልሳቸዋለሁ፤ እነርሱም ያፈራሉ ይበዙማል።
- 4
የሚጠብቋቸውን እረኞች አስነሣላቸዋለሁ፥ ዳግመኛም አይፈሩምና አይደነግጡም፥ ከእነሱም አንድ አይጐድልም፥ ይላል እግዚአብሔር።
- 5
እነሆ፥ ለዳዊት ጻድቅ ቍጥቋጥ የማስነሣበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር፥ እርሱም እንደ ንጉሥ ይነግሣል፥ ይከናወንለታልም፥ በምድርም ፍርድንና ጽድቅን ያደርጋል።
- 6
በዘመኑም ይሁዳ ይድናል እስራኤልም ተዘልሎ ይቀመጣል፥ የሚጠራበትም ስም። እግዚአብሔር ጽድቃችን ተብሎ ነው።
- 7
ስለዚህ፥ እነሆ። የእስራኤልን ልጆች ከግብጽ ምድር ያወጣ ሕያው እግዚአብሔርን! ዳግመኛ የማይባልበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር፤
- 8
ነገር ግን። የእስራኤልን ቤት ዘር ከሰሜን አገርና ካሰደድኋቸውም አገር ሁሉ ያወጣና የመራ ሕያው እግዚአብሔርን! ይባላል፤ በምድራቸውም ይቀመጣሉ።
- 9
ስለ ነቢያት፤ ልቤ በውስጤ ተሰብሮአል አጥንቶቼም ሁሉ ታውከዋል፤ ከእግዚአብሔር የተነሣ ከቅዱስ ቃሉም የተነሣ የወይን ጠጅ እንዳሸነፈው እንደ ሰካራም ሰው ሆኛለሁ።
- 10
ምድር ከአመንዝሮች ተሞልታለችና፥ ከመርገምም የተነሣ ምድር አልቅሳለች፤ የምድረ በዳ ማሰማርያ ደርቆአል፤ አካሄዳቸው ክፉ ነው፥ ብርታታቸውም ቅን አይደለም።
- 11
ነቢዩና ካህኑም ረክሰዋልና፥ በቤቴም ውስጥ ክፋታቸውን አግኝቻለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
- 12
ስለዚህ መንገዳቸው በጨለማ እንዳለች እንደ ድጥ ስፍራ ትሆንባቸዋለች፥ እነርሱም ፍግምግም ብለው ይወድቁባታል፤ እኔም በምጐበኛቸው ዓመት ክፉ ነገርን አመጣባቸዋለሁና፥ ይላል እግዚአብሔር።
- 13
በሰማርያ ነቢያት ላይ ስንፍናን አይቻለሁ፤ በበኣል ትንቢት ይናገሩ ነበር፥ ሕዝቤንም እስራኤል ያስቱ ነበር።
- 14
በኢየሩሳሌምም ነቢያት ላይ የሚያስደነግጥን ነገር አይቻለሁ፤ ያመነዝራሉ በሐሰትም ይሄዳሉ፤ ማንም ከክፋቱ እንዳይመለስ የክፉ አድራጊዎችን እጅ ያበረታሉ፤ ሁሉም እንደ ሰዶም የሚኖሩባትም እንደ ገሞራ ሆኑብኝ።
- 15
ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ከኢየሩሳሌም ነቢያት ዘንድ ርኵሰት በምድር ሁሉ ላይ ወጥቶአልና እሬትን አበላቸዋለሁ የሐሞትንም ውኃ አጠጣቸዋለሁ።
- 16
የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ትንቢት የሚናገሩላችሁን የነቢያትን ቃል አትሰሙ፤ ከንቱነትን ያስተምሩአችኋል፤ ከእግዚአብሔር አፍ ሳይሆን ከገዛ ልባቸው የወጣውን ራእይ ይናገራሉ።
- 17
ለሚንቁኝ ሁልጊዜ። እግዚአብሔር። ሰላም ይሆንላችኋል ብሎአል ይላሉ፤ በልቡም እልከኝነት ለሚሄድ ሁሉ። ክፉ ነገር አያገኛችሁም ይላሉ።
- 18
ቃሉን ያይና ይሰማ ዘንድ በእግዚአብሔር ምክር የቆመ ማን ነውና? ቃሉንስ ያደመጠ የሰማስ ማን ነው?
- 19
እነሆ፥ የእግዚአብሔር ዐውሎ ነፋስ፥ እርሱም ቍጣው፥ የሚያገለባብጥ ዐውሎ ነፍስ ወጥቶአል፤ የዓመፀኞችን ራስ ይገለባብጣል።
- 20
የእግዚአብሔር ቍጣ የልቡን አሳብ ሠርቶ እስኪፈጽም ድረስ አይመለስም፤ በኋለኛው ዘመን ፈጽማችሁ ታስተውሉታላችሁ።
- 21
እኔ ሳልልካቸው እነዚህ ነቢያት ሮጡ፤ እኔም ሳልነግራቸው ትንቢትን ተናገሩ።
- 22
በምክሬ ግን ቢቆሙ ኖሮ፥ ለሕዝቤ ቃሌን ባሰሙ ነበር፥ ከክፉም መንገዳቸው ከሥራቸውም ክፋት በመለሱአቸው ነበር።
- 23
እኔ የቅርብ አምላክ ነኝ እንጂ የሩቅ አምላክ አይደለሁም።
- 24
ሰው በስውር ቢሸሸግ፥ እኔ አላየውምን? ሰማይንና ምድርንስ የሞላሁ እኔ አይደለሁምን? ይላል እግዚአብሔር።
- 25
አለምሁ አለምሁ እያሉ በስሜ ሐሰትን የሚናገሩትን የነቢያትን ነገር ሰምቻለሁ።
- 26
ትንቢትን በሐሰት በሚናገሩ፥ የልባቸውንም ሽንገላ በሚናገሩ በነቢያት ልብ ይህ የሚሆነው እስከ መቼ ነው?
- 27
አባቶቻቸው ስለ በኣል ስሜን እንደ ረሱ፥ እያንዳንዱ ለባልንጀራው በሚናገራት ሕልማቸው ሕዝቤ ስሜን ለማስረሳት ያስባሉ።
- 28
የሚያልም ነቢይ ሕልምን ይናገር፤ ቃሌም ያለበት ቃሌን በእውነት ይናገር። ገለባ ከስንዴ ጋር ምን አለው?
- 29
በውኑ ቃሌ እንደ እሳት፥ ድንጋዩንም እንደሚያደቅቅ መዶሻ አይደለችምን? ይላል እግዚአብሔር።
- 30
ስለዚህ፥ እነሆ፥ እያንዳንዱ ከባልንጀራው ዘንድ ቃሌን በሚሰርቁ ነቢያት ላይ ነኝ፥ ይላል እግዚአብሔር።
- 31
እነሆ፥ ከምላሳቸው ትንቢትን አውጥተው። እርሱ ይላል በሚሉ ነቢያት ላይ ነኝ፥ ይላል እግዚአብሔር።
- 32
እነሆ፥ ሐሰትን በሚያልሙ በሚናገሩም በሐሰታቸውና በድፍረታቸውም ሕዝቤን በሚያስቱ በነቢያት ላይ ነኝ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ እኔም አልላክኋቸውም አላዘዝኋቸውምም ለእነዚህም ሕዝብ በማናቸውም አይረቡአቸውም፥ ይላል እግዚአብሔር።
- 33
ይህ ሕዝብ ወይም ነቢይ ወይም ካህን። የእግዚአብሔር ሸክም ምንድር ነው? ብሎ ቢጠይቅህ፥ አንተ። ሸክሙ እናንተ ናችሁ፥ እጥላችሁማለህ፥ ይላል እግዚአብሔር ትላቸዋለህ።
- 34
የእግዚአብሔር ሸክም የሚለውን ነቢይንና ካህንን ሕዝቡንም ያን ሰውና ቤቱን እቀጣለሁ።
- 35
አንዱም አንዱ ለባልንጀራው፥ አንዱም አንዱ ለወንድሙ እንዲህ ይበል። እግዚአብሔር የመለሰው ምንድር ነው? እግዚአብሔርስ ምን ነገር ተናገረ?
- 36
ለሰው ሁሉ ቃል ሸክም ይሆንበታልና የእግዚአብሔር ሸክም ይሆንበታልና የእግዚአብሔር ሸክም ብላችሁ ከእንግዲህ ወዲህ አትጥሩ፤ የሠራዊትን ጌታ የአምላካችንን የእግዚአብሔርን የሕያውን አምላክ ቃል ለውጣችኋልና።
- 37
ለነቢዩ። እግዚአብሔር ምን መለሰልህ? እግዚአብሔርስ የተናገረው ምንድር ነው? ትላለህ።
- 38
ነገር ግን። የእግዚአብሔር ሸክም ብትሉ፥ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እኔ። የእግዚአብሔር ሸክም አትበሉ ብዬ ልኬባችኋለሁና፥ እናንተም ይህን ቃል።
- 39
የእግዚአብሔር ሸክም ብላችኋልና ስለዚህ፥ እነሆ፥ ፈጽሜ እረሳችኋለሁ እናንተንም ለእናንተና ለአባቶቻችሁም የሰጠኋትን ከተማ ከፊቴ እጥላለሁ።
- 40
የዘላለምንም ስድብ ከቶም ተረስቶ የማይጠፋውን የዘላለምን እፍረት አመጣባችኋለሁ።