Jeremiah 17
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
የይሁዳ ኃጢአት በብረት ብርዕና በተሾለ ዕብነ አልማዝ ተጽፎአል፤ በልባቸው ጽላትና በመሠዊያቸው ቀንዶች ተቀርጾአል።
- 2
ልጆቻቸውም ከለመለሙ ዛፎች በታችና በረዘሙት ኮረብቶች ላይ ያሉትን መሠዊያቸውንና የማምለኪያ ዐፀዳቸውን ያስባሉ።
- 3
በሜዳ ያለው ተራራዬ ሆይ፥ ባለጠግነትህንና መዝገብህን ሁሉ የኮረብታውን መስገጃዎችህም ስለ ኃጢአት በድንበሮችህ ሁሉ ለመበዝበዝ እሰጣለሁ።
- 4
አንተም የሰጠሁህን ርስት ትለቅቃለህ ለዘላለምም በማታውቃትም ምድር ለጠላቶቻችሁ ባሪያ አደርግሃለሁ፤ ለዘላለም የሚነድደውን እሳት በቍጣዬ አንድዳችኋልና።
- 5
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በሰው የሚታመን ሥጋ ለባሹንም ክንዱ የሚያደርግ ልቡም ከእግዚአብሔር የሚመለስ ሰው ርጉም ነው።
- 6
በምድረ በዳ እንዳለ ቍጥቋጦ ይሆናል፥ መልካምም በመጣ ጊዜ አያይም፤ ሰውም በሌለበት፥ ጨው ባለበት ምድር በምድረ በዳ በደርቅ ስፍራ ይቀመጣል።
- 7
በእግዚአብሔር የታመነ እምነቱም እግዚአብሔር የሆነ ሰው ቡሩክ ነው።
- 8
በውኃ አጠገብ እንደ ተተከለ፥ በወንዝም ዳር ሥሩን እንደሚዘረጋ ሙቀትም ሲመጣ እንደማይፈራ ቅጠሉም እንደሚለመልም፥ በድርቅ ዓመትም እንደማይሠጋ ፍሬውንም እንደማያቋርጥ ዛፍ ይሆናል።
- 9
የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ እጅግም ክፉ ነው፤ ማንስ ያውቀዋል?
- 10
እኔ እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ እንደ መንገዱ፥ እንደ ሥራው ፍሬ እሰጥ ዘንድ ልብን እመረምራለሁ ኵላሊትንም እፈትናለሁ።
- 11
ያልወለደችውን እንደምታቅፍ ቆቅ፥ እንዲሁ በቅን ሳይሆን ባለጠግነትን የሚሰበስብ ሰው ነው፤ በእኩሌታ ዘመኑ ይተወዋል፥ በፍጻሜውም ሰነፍ ይሆናል።
- 12
የመቅደሳችን ስፍራ ከጥንት ጀምሮ ክፍ ያለ የክብር ዙፋን ነው።
- 13
አቤቱ፥ የእስራኤል ተስፋ ሆይ፥ የሚተዉህ ሁሉ ያፍራሉ፤ ከአንተም የሚለዩ የሕይወትን ውኃ ምንጭ እግዚአብሔርን ትተዋልና በምድር ላይ ይጻፋሉ።
- 14
አቤቱ፥ ፈውሰኝ እኔም እፈወሳለሁ፤ አድነኝ እኔም እድናለሁ፤ አንተ ምስጋናዬ ነህና።
- 15
እነሆ። የእግዚአብሔር ቃል ወዴት አለች? አሁን ትምጣ ይሉኛል።
- 16
እኔም አንተን ተከትዬ እረኛ ከመሆን አልቸኰልሁም፥ የመከራንም ቀን አልወደድሁም፤ አንተ ታውቃለህ፤ ከከንፈሬ የወጣው በፊትህ ነበረ።
- 17
ለማስፈራራት አትሁንብኝ፤ በመከራ ቀን አንተ መጠጊያዬ ነህ።
- 18
አሳዳጆቼ ይፈሩ፥ እኔ ግን አልፈር፤ እነርሱ ይደንግጡ፥ እኔ ግን አልደንግጥ፤ ክፉንም ቀን አምጣባቸው፥ በሁለት እጥፍ ጥፋት አጥፋቸው።
- 19
እግዚአብሔር እንዲህ ይለኛል። ሂድ፥ የይሁዳም ነገሥታት በሚገቡበትና በሚወጡበት በሕዝቡ ልጆች በር በኢየሩሳሌምም በሮች ሁሉ ቁም፤
- 20
እንዲህም በላቸው። በእነዚህ በሮች የምትገቡ፥ እናንተ የይሁዳ ነገሥታት፥ ይሁዳም ሁሉ፥ በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሁሉ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ።
- 21
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፥ በሰንበትም ቀን ሸክም አትሸከሙ፥ በኢየሩሳሌምም በሮች አታግቡ፥
- 22
ከቤቶቻችሁም በሰንበት ቀን ሸክምን አታውጡ፥ ሥራንም ሁሉ አትሥሩበት፤ አባቶቻችሁንም እንዳዘዝሁ የሰንበትን ቀን ቀድሱ።
- 23
እነርሱ ግን አልሰሙም ጆሮአቸውን አላዘነበሉም፥ እንዳይሰሙና እንዳይገሠጹም አንገታቸውን አደነደኑ።
- 24
እኔን ፈጽሞ ብትሰሙ፤ ይላል እግዚአብሔር፥ በሰንበትም ቀን በዚህች ከተማ በሮች ሸክም ባታገቡ፥ የሰንበትንም ቀን ብትቀድሱ ሥራንም ሁሉ ባትሠሩበት፥
- 25
በዳዊት ዙፋን ላይ የሚቀመጡ ነገሥታትና መሳፍንት በሰረገሎችና በፈረሶች ላይ እየተቀመጡ በዚህች ከተማ በሮች ይገባሉ፤ እነርሱና መሳፍንቶቻቸው የይሁዳም ሰዎች በኢየሩሳሌምም የሚቀመጡ ይገባሉ፥ ይህችም ከተማ ለዘላለም የሰው መኖሪያ ትሆናለች።
- 26
የሚቃጠለው መሥዋዕትና ሌላ መሥዋዕትን የእህሉንም ቍርባን ዕጣኑንም የምስጋናውንም መሥዋዕት ይዘው ከይሁዳ ከተሞች ከኢየሩሳሌምም ዙሪያ ከብንያምም አገር ከቈላውም ከደጋውም ከደቡብም ወደ እግዚአብሔር ቤት ይመጣሉ።
- 27
ነገር ግን የሰንበትን ቀን እንድትቀድሱ፥ በሰንበትም ቀን ሸክምን ተሸክማችሁ በኢየሩሳሌም በሮች እንዳትገቡ የነገርኋችሁን ባትሰሙኝ፥ በበሮችዋ ላይ እሳትን አነድዳለሁ፥ የኢየሩሳሌምንም አዳራሾች ትበላለች፥ አትጠፋም።