Jeremiah 14
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
ወደ ኤርምያስ ስለ ድርቅ የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው።
- 2
ይሁዳ አለቀሰች፥ ደጆችዋም ባዶ ሆኑ በምድርም ላይ ጨለሙ፤ የኢየሩሳሌም ጩኸት ከፍ ከፍ ብሎአል።
- 3
ታላላቆችም ብላቴኖቻቸውን ወደ ውኃ ሰደዱ፤ ወደ ጕድጓድ መጡ ውኃም አላገኙም፥ ዕቃቸውንም ባዶውን ይዘው ተመለሱ፤ አፈሩም ተዋረዱም ራሳቸውንም ተከናነቡ።
- 4
በምድር ላይ አልዘነበምና መሬቱ ስንጥቅጥቅ ስለሆነ አራሾች አፈሩ ራሳቸውንም ተከናነቡ።
- 5
ዋላ ደግሞ በምድረ በዳ ወለደች፥ ሣርም የለምና ግልገልዋን ተወች።
- 6
የሜዳ አህዮችም በወና ኮረብታ ላይ ቆመዋል፥ እንደ ቀበሮም ወደ ነፋስ አለከለኩ፤ ልምላሜም የለምና ዓይኖቻቸው ጠወለጉ።
- 7
አቤቱ፥ ኃጢአታችን ብዙ ነውና፥ በአንተም ላይ ኃጢአት ሠርተናልና ኃጢአታችን ይመሰክርብናል ነገር ግን ስለ ስምህ ብለህ አድርግ።
- 8
አንተ የእስራኤል ተስፋ ሆይ በመከራም ጊዜ የምታድነው፥ በምድር እንደ እንግዳ፥ ወደ ማደሪያ ዘወር እንደሚል መንገደኛ ስለ ምን ትሆናለህ?
- 9
እንዳንቀላፋ ሰው ሰው፥ ያድንም ዘንድ እንደማይችል ኃያል ስለ ምን ትሆናለህ? አንተ ግን፥ አቤቱ፥ በመካከላችን ነህ እኛም በስምህ ተጠርተናል፤ አትተወን።
- 10
እግዚአብሔር ለዚህ ሕዝብ እንዲህ ይላል። መቅበዝበዝን ወድደዋል እግራቸውንም አልከለከሉም፤ ስለዚህ እግዚአብሔር በእነርሱ ደስ አይለውም፥ በደላቸውንም አሁን ያስባል ኃጢአታቸውንም ይቀጣል።
- 11
እግዚአብሔርም። ለዚህ ሕዝብ ስለ መልካም አትጸልይላቸው።
- 12
በጾሙ ጊዜ ጸሎታቸውን አልሰማም፤ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን ባቀረቡ ጊዜ አልቀበላቸውም፤ በሰይፍና በራብ በቸነፈርም አጠፋቸዋለሁ አለኝ።
- 13
እኔም። ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ወዮ! እነሆ፥ ነቢያት። በእውነት ሰላምን በዚህ ስፍራ እሰጣችኋለሁ እንጂ ሰይፍን አታዩም፥ ራብም አያገኛችሁም ይሉአቸዋል አልሁ።
- 14
እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ። ነቢያቱ ውሸት በስሜ ትንቢት ይናገራሉ፤ አላክኋቸውም፥ አላዘዝኋቸውም፥ አልተናገርኋቸውም፤ የውሸቱን ራእይ ምዋርትንም ከንቱንም ነገር የልባቸውንም ሽንገላ ይሰብኩላችኋል።
- 15
ስለዚህ እግዚአብሔር በስሜ ትንቢት ስለሚናገሩ ነቢያት። በዚህች አገር ሰይፍና ራብ አይሆንም ስለሚሉ ስላላክኋቸው ነቢያት እንዲህ ይላል። እነዚያ በሰይፍና በራብ ይጠፋሉ።
- 16
ትንቢት የሚናገሩላቸውም ሰዎች ከራብና ከሰይፍ የተነሣ በኢየሩሳሌም አደባባይ ይበተናሉ፤ ክፋታቸውንም አፈስስባቸዋለሁ እነርሱንና ሚስቶቻቸውን ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውንም የሚቀብራቸው አይገኝም።
- 17
እንደዚህም ብለህ ትነግራቸዋለህ። የወገኔ ልጅ ድንግሊቱ በታላቅ ስብራትና እጅግ ክፉ በሆነ ቍስል ተሰብራለችና ዓይኖቼ ሌሊትና ቀን ሳያቋርጡ እንባ ያፈሳሉ።
- 18
ወደ ሜዳ ብወጣ፥ እነሆ፥ በሰይፍ የሞቱ አሉ፤ ወደ ከተማም ብገባ፥ እነሆ፥ በራብ የከሱ አሉ፤ ነቢዩና ካህኑም ወደማያውቋት አገር ሄደዋልና።
- 19
በውኑ ይሁዳን ፈጽመህ ጥለኸዋልን? ነፍስህስ ጽዮንን ጠልታታለችን? ስለ ምን መታኸን? ፈውስስ ስለ ምን የለንም? ሰላምን በተስፋ ተጠባበቅን፥ መልካምም አልተገኘም፤ ፈውስን በተስፋ ተጠባበቅን፥ እነሆም፥ ድንጋጤ ሆነ።
- 20
አቤቱ፥ በአንተ ላይ ኃጢአትን ሠርተናልና ክፋታችንንና የአባቶቻችንን በደል እናውቃለን።
- 21
ስለ ስምህ ብለህ አትናቀን፥ የክብርህንም ዙፋን አታስነውር፤ ከእኛ ጋርም ያደረግኸውን ቃል ኪዳንህን አስብ እንጂ አታፍርስ።
- 22
በውኑ በአሕዛብ ጣዖታት መካከል ያዘንብ ዘንድ የሚችል ይገኛልን? ወይስ ሰማይ ዝናብ ማፍሰስ ይችላልን? አቤቱ አምላካችን ሆይ፥ አንተ አይደለህምን? አንተ ይህን ነገር ሁሉ አድርገሃልና ስለዚህ አንተን በተስፋ እንጠባበቃለን።