Jeremiah 12
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
አቤቱ፥ ከአንተ ጋር በተምዋገትሁ ጊዜ አንተ ጻድቅ ነህ፤ ነገር ግን ከአንተ ጋር ስለ ፍርድ ልናገር። የኃጢአተኞች መንገድ ስለምን ይቃናል? በደልንስ ለሚያደርጉ ሁሉ ስለምን ደኅንነት ይሆናል?
- 2
ተክለሃቸዋል፤ ሥር ሰድደዋል፤ አድገዋል አፍርተውማል፤ በአፋቸው አንተ ቅርብ ነህ፥ ከልባቸው ግን ሩቅ ነህ።
- 3
አንተ ግን፥ አቤቱ፥ አውቀኸኛል፤ አይተኸኛል፥ ልቤንም በፊትህ ፈትነሃል፤ እንደ በጎች ለመታረድ ጐትተህ ለያቸው፥ ለመታረድም ቀን አዘጋጃቸው።
- 4
ምድሪቱ የምታለቅሰው፥ የአገሩ ሣርስ ሁሉ የሚደርቀው እስከ መቸ ነው? የተቀመጡባት ሰዎች። ፍጻሜያችንን አያይም ብለዋልና ስለ ክፋታቸው እንስሶችና ወፎች ጠፍተዋል።
- 5
ከእግረኞች ጋር በሮጥህ ጊዜ እነርሱ ቢያደክሙህ፥ ከፈረሶች ጋር መታገል እንዴት ትችላለህ? በሰላምም ምድር ታምነህ ብትቀመጥ፥ በዮርዳኖስ ትዕቢት እንዴት ታደርጋለህ?
- 6
ወንድሞችህና የአባትህ ቤት እነርሱ ጭምር አታልለውሃልና፥ በኋላህም ጮኸዋልና፤ በመልካምም ቢናገሩህም አትታመናቸው።
- 7
ቤቴን ትቼአለሁ ርስቴንም ጥያለሁ፥ ነፍሴም የምትወድዳትን በጠላቶችዋ እጅ አሳልፌ ሰጥቻለሁ።
- 8
ርስቴ በዱር እንዳለ አንበሳ ሆናብኛለች፤ ድምፅዋን አንሥታብኛለች፤ ስለዚህ ጠልቻታለሁ።
- 9
ርስቴ እንደ ዝንጕርጕር አሞራ ሆነችብኝን? አሞሮችስ በዙሪያዋና በላይዋ ሆነዋልን? ሂዱ፥ የምድር አራዊትን ሁሉ ሰብስቡ፥ ይበሉም ዘንድ አምጡአቸው።
- 10
ብዙ እረኞች የወይኑን ቦታዬን አጥፍተዋል፥ እድል ፈንታዬንም ረግጠዋል፤ የአምሮቴን እድል ፈንታ ምድረ በዳ አድርገውታል።
- 11
ባድማ አድርገውታል፥ ፈርሶም ወደ እኔ ያለቅሳል፤ ምድር ሁሉ ባድማ ሆናለች በልቡም የሚያስባት የለም።
- 12
በወናዎች ኮረብቶች ሁሉ ላይ በዝባዦች መጥተዋል፥ የእግዚአብሔር ሰይፍ ከምድር ዳር ጀምሮ እስከ ምድር ዳር ድረስ ይበላልና፤ ለሥጋ ለባሽ ሁሉ ሰላም የለም።
- 13
ስንዴን ዘሩ እሾህንም አጨዱ፤ ደከሙ፥ ምንም አልረባቸውም፤ ስለ እግዚአብሔር ጽኑ ቍጣ ከፍሬያችሁ ታፍራላችሁ።
- 14
እግዚአብሔር ለሕዝቤ ለእስራኤል ያወረስሁትን ርስት ለሚነኩት ክፉዎች ጐረቤቶች ሁሉ እንዲህ ይላልና። እነሆ፥ ከምድራቸው እነቅላቸዋለሁ፥ የይሁዳንም ቤት ከመካከላቸው እነቅለዋለሁ።
- 15
ከነቀልኋቸውም በኋላ መልሼ እምራቸዋለሁ፥ እያንዳንዱንም ወደ ርስቱ እያንዳንዱንም ወደ ምድሩ እመልሳለሁ።
- 16
በበኣል ይምሉ ዘንድ ሕዝቤን እንዳስተማሩ በስሜ። ሕያው እግዚአብሔርን! ብለው ይምሉ ዘንድ የሕዝቤን መንገድ በትጋት ቢማሩ፥ በዚያን ጊዜ በሕዝቤ መካከል ይመሠረታሉ።
- 17
ባይሰሙኝ ግን ያንን ሕዝብ ፈጽሜ እነቅለዋለሁ አጠፋውማለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።