Judges 10
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
ከአቤሜሌክም በኋላ ከይሳኮር ነገድ የሆነ የዱዲ ልጅ የፎሖ ልጅ ቶላ እስራኤልን ለማዳን ተነሣ፤ በተራራማውም በኤፍሬም አገር ባለችው በሳምር ተቀምጦ ነበር።
- 2
በእስራኤልም ላይ ሀያ ሦስት ዓመት ፈረደ፤ ሞተም፥ በሳምርም ተቀበረ።
- 3
ከእርሱም በኋላ ገለዓዳዊው ኢያዕር ተነሣ፥ በእስራኤልም ላይ ሀያ ሁለት ዓመት ፈረደ።
- 4
በሠላሳ የአህያ ግልገሎች ይቀመጡ የነበሩ ሠላሳ ልጆችም ነበሩት፤ ለእነርሱም እስከ ዛሬ ድረስ የኢያዕር መንደሮች የተባሉ በገለዓድ ምድር ያሉ ሠላሳ ከተሞች ነበሩአቸው።
- 5
ኢያዕርም ሞተ፥ በቃሞንም ተቀበረ።
- 6
የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት እንደ ገና ክፉ ሥራ ሠሩ በኣሊምንና አስታሮትን የሶርያንም አማልክት፥ የሲዶናንም አማልክት፥ የሞዓብንም አማልክት፥ የአሞንንም ልጆች አማልክት፥ የፍልስጥኤማውያንንም አማልክት አመለኩ፤ እግዚአብሔርንም ተዉ፥ አላመለኩትምም።
- 7
የእግዚአብሔርም ቍጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፥ በፍልስጥኤማውያንና በአሞን ልጆች እጅ አሳልፎ ሰጣቸው።
- 8
በዚያም ዓመት የእስራኤልን ልጆች ሥቃይ አበዙባቸው፤ በዮርዳኖስ ማዶ በአሞራውያን አገር በገለዓድ ውስጥ ያሉትን የእስራኤልን ልጆች ሁሉ አሥራ ስምንት ዓመት ተጋፉአቸው።
- 9
የአሞንም ልጆች ከይሁዳ ከብንያምና ከኤፍሬም ቤት ጋር ደግሞ ሊዋጋ ዮርዳኖስን ተሻገሩ፤ እስራኤልም እጅግ ተጨነቁ።
- 10
የእስራኤልም ልጆች። አምላካችንን ትተን በኣሊምን አምልከናልና አንተን በድለናል ብለው ወደ እግዚአብሔር ጮኹ።
- 11
እግዚአብሔርም የእስራኤልን ልጆች አላቸው። ግብፃውያን፥ አሞራውያንም፥ የአሞንም ልጆች፥
- 12
ፍልስጥኤማውያንም፥ ሲዶናውያንም፥ አማሌቃውያንም፥ ማዖናውያንም አላስጨነቋችሁምን? ወደ እኔም ጮኻችሁ፥ እኔም ከእጃቸው አዳንኋችሁ።
- 13
እናንተ ግን ተዋችሁኝ ሌሎችንም አማልክት አመለካችሁ፤ ስለዚህም ደግሞ አላድናችሁም።
- 14
ሄዳችሁም የመረጣችኋቸውን አማልክት ጥሩ፤ እነርሱም በመከራችሁ ጊዜ ያድኑአችሁ።
- 15
የእስራኤልም ልጆች እግዚአብሔርን። እኛ ኃጢአትን ሠርተናል፤ አንተ ደስ የሚያሰኝህን አድርግብን ዛሬ ግን፥ እባክህ፥ አድነን አሉት።
- 16
ሌሎችንም አማልክት ከመካከላቸው አስወገዱ፥ እግዚአብሔርንም አመለኩ፤ ነፍሱም ስለ እስራኤል ጕስቍልና አዘነች።
- 17
የአሞንም ልጆች ተሰብስበው በገለዓድ ሰፈሩ። የእስራኤልም ልጆች ተሰብስበው በምጽጳ ሰፈሩ።
- 18
ሕዝቡም፥ የገለዓድ አለቆች፥ እርስ በእርሳቸው። ከአሞን ልጆች ጋር መዋጋት የሚጀምር ማን ነው? እርሱ በገለዓድ ሰዎች ሁሉ ላይ አለቃ ይሆናል አሉ። a