Hosea 7
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
በሐሰት አድርገዋልና፥ ሌባም ገብቶአልና፥ በውጭም ወንበዴዎች ቀምተዋልና እስራኤልን እፈውስ ዘንድ በወደድሁ ጊዜ የኤፍሬም ኃጢአትና የሰማርያ ክፋት ተገለጠ።
- 2
እኔም ክፋታቸውን ሁሉ እንዳሰብሁ በልባቸው አያስቡም አሁንም ሥራቸው ከብባቸዋለች፥ በፊቴም አለች።
- 3
ንጉሡን በክፋታቸው፥ አለቆቹንም በሐሰታቸው ደስ አሰኝተዋል።
- 4
ሁሉም አመንዝራዎች ናቸው፤ ጋጋሪ እንደሚያነድድበት እንደ ምድጃ ናቸው፤ ሁሉ እስኪቦካ ድረስ እሳትን መቈስቈስና እርሾን መለወስ ይቆያል።
- 5
በንጉሣችን ቀን አለቆች ከወይን ጠጅ ሙቀት የተነሣ ታመሙ፤ እርሱም ከዋዘኞች ጋር እጁን ዘረጋ።
- 6
እያደቡ ልባቸውን እንደ ምድጃ አዘጋጅተዋል፤ አበዛቸውም ሌሊቱን ሁሉ አንቀላፋ፤ በጠባም ጊዜ እንደ እሳት ነበልባል ይነድዳል።
- 7
ሁሉም እንደ ምድጃ ግለዋል፥ ፈራጆቻቸውንም በሉ፤ ነገሥታቶቻቸውም ሁሉ ወደቁ፤ ከእነርሱም ወደ እኔ የሚጮኽ የለም።
- 8
ኤፍሬም ከአሕዛብ ጋር ተደባለቀ፤ ኤፍሬም እንዳልተገላበጠ ቂጣ ነው።
- 9
እንግዶች ጕልበቱን በሉት፥ እርሱም አላወቀም፤ ሽበትም ወጣበት፥ እርሱም አላወቀም።
- 10
የእስራኤልም ትዕቢቱ በፊቱ መሰከረ፤ ወደ አምላካቸው ወደ እግዚአብሔር ግን አልተመለሱም፥ በዚህም ሁሉ አልፈለጉትም።
- 11
ኤፍሬምም አእምሮ እንደሌላት እንደ ሰነፍ ርግብ ነው፤ ግብጽን ጠሩ፥ ወደ አሦርም ሄዱ።
- 12
ሲሄዱ አሽክላዬን አዘረጋባቸዋለሁ፤ እንደ ሰማይ ወፎች አወርዳቸዋለሁ፤ መከራቸውን ሲሰሙ እገሥጻቸዋለሁ።
- 13
ከእኔ ፈቀቅ ብለዋልና ወዮላቸው! በእኔም ላይ ዐመፀዋልና ጥፋት ይምጣባቸው! እኔ ልታደጋቸው ወደድሁ፥ እነርሱ ግን በሐሰት ተናገሩብኝ።
- 14
በመኝታቸው ላይ ሆነው ያለቅሱ ነበር እንጂ በልባቸው ወደ እኔ አልጮኹም፤ ስለ እህልና ስለ ወይን ጠጅ ይሰበሰቡ ነበር፤ በእኔም ላይ ዐመፁ።
- 15
እኔም ክንዳቸውን አስተማርሁና አጸናሁ፤ እነርሱ ግን ክፉ ነገርን መከሩብኝ።
- 16
ወደ ከንቱ ነገር ተመለሱ፤ እንደ ተንኰለኛ ቀስት ሆኑ፤ አለቆቻቸው ከምላሳቸው ቍጣ የተነሣ በሰይፍ ይወድቃሉ፤ ይህ በግብጽ ምድር ውስጥ መሳለቂያ ይሆንባቸዋል።