Hosea 5
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
ካህናት ሆይ፥ ይህን ስሙ፤ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ አድምጡ፤ የንጉሥ ቤት ሆይ፥ ልብ አድርጉ፤ በምጽጳ ላይ ወጥመድ፥ በታቦርም ላይ የተዘረጋ አሽክላ ሆናችኋልና ፍርድ በእናንተ ላይ ነው።
- 2
ዓመፀኞችም እርድ አብዝተዋል፤ እኔ ግን እነዚያን ሁሉ እዘልፋለሁ።
- 3
ኤፍሬምን አውቀዋለሁ፥ እስራኤልም ከእኔ አልተሰወረም፤ ኤፍሬም ሆይ፥ ዛሬ አመንዝረሃል፥ እስራኤልም ረክሶአል።
- 4
ወደ አምላካቸው ይመለሱ ዘንድ ሥራቸውን አላቀኑም፤ የግልሙትና መንፈስ በውስጣቸው አለና፤ እግዚአብሔርንም አላውቁምና።
- 5
የእስራኤልም ትዕቢት በፊቱ ይመሰክራል፤ ስለዚህ እስራኤልና ኤፍሬም በኃጢአታቸው ይሰናከላሉ፤ ይሁዳም ደግሞ ከእነሱ ጋር ይሰናከላል።
- 6
እግዚአብሔርንም ለመሻት በጎቻቸውንና ላሞቻቸውን ነድተው ይሄዳሉ፤ ነገር ግን እርሱ ከእነርሱም ተመልሶአልና አያገኙትም።
- 7
ዲቃሎችን ልጆች ወልደዋልና እግዚአብሔርን ወንጅለዋል፤ አሁንም አንድ ወር እነርሱንና ርስታቸውን ይበላቸዋል።
- 8
በጊብዓ መለከትን፥ በራማ እንቢልታን ንፉና። ብንያም ሆይ፥ ከአንተ በኋላ እያላችሁ በቤትአዌን ላይ እሪ በሉ።
- 9
ኤፍሬም በዘለፋ ቀን የፈረሰ ይሆናል። በእስራኤል ነገዶች ዘንድ በእርግጥ የሚሆነውን ነገር ገልጫለሁ።
- 10
የይሁዳ አለቆች ድምበርን እንደሚነቅሉ ሆነዋል፤ እኔም መዓቴን እንደ ውኃ አፈስስባቸዋለሁ።
- 11
ኤፍሬም ከትእዛዝ በኋላ መሄድን ወድዶአልና የተገፋና በፍርድ የተጐዳ ሆኖአል።
- 12
እኔም ለኤፍሬም እንደ ብል፥ ለይሁዳም ቤት እንደ ነቀዝ ሆኜአለሁ።
- 13
ኤፍሬምም ደዌውን፥ ይሁዳም ቍስሉን ባየ ጊዜ ኤፍሬም ወደ አሦር ሄደ ወደ ንጉሡም ወደ ኢያሪም መልእክተኛን ላከ፤ እርሱ ግን ይፈውሳችሁ ዘንድ፥ ከቊስላችሁም ያድናችሁ ዘንድ አልቻለም።
- 14
እኔም ለኤፍሬም እንደ አንበሳ፥ ለይሁዳም ቤት እንደ አንበሳ ደቦል እሆናለሁና፤ እኔም ነጥቄ እሄዳለሁ እወስድማለሁ፥ የሚያድንም አይገኝም።
- 15
በደላቸውንም እስኪያውቁ ድረስ፥ ፊቴንም እስኪሹ ድረስ ሄጄ ወደ ስፍራዬ እመለሳለሁ፤ በመከራቸው ጊዜ እጅግ አድርገው ፊቴን ይፈልጋሉ።