Hosea 10
World English Bible (en) → Amharic Bible (am)
- 1
እስራኤል ፍሬው የበዛለት የለመለመ ወይን ነው፤ እንደ ፍሬው ብዛት መሠዊያውን አብዝቶአል፤ እንደ ምድሩም ማማር መጠን ሐውልቶችን እያሳመሩ ሠርተዋል።
- 2
ልባቸው ተከፈለ፤ አሁንም በደላቸውን ይሸከማሉ፤ እርሱ መሠዊያቸውን ያፈርሳል፥ ሐውልቶቻቸውን ያጠፋል።
- 3
አሁንም። ንጉሥ የለንም፥ እግዚአብሔርን አልፈራንምና፤ ንጉሥስ ምን ያደርግልናል? ይላሉ።
- 4
የማይረባውን ቃል ይናገራሉ፤ ቃል ኪዳን በገቡ ጊዜ በሐሰት ይምላሉ፤ ስለዚህ መርዛም ሣር በእርሻ ትልም ላይ እንደሚበቅል መቅሠፍት ይበቅልባቸዋል።
- 5
የሰማርያ ሰዎች ስለ ቤትአዌን እምቦሳ ይፈራሉ፤ ክብሩም ከእርሱ ዘንድ ወጥቶአልና ሕዝቡ ያለቅሱለታል፥ የጣዖቱ ካህናትም በኀዘን ይንተባተባሉ።
- 6
ለንጉሡ ለኢያሪም እጅ መንሻ ይሆን ዘንድ ወደ አሦር ይማረካል፤ ኤፍሬምን እፍረት ይይዘዋል፥ እስራኤልም በምክሩ ያፍራል።
- 7
ሰማርያ ከንጉሥዋ ጋር በውኃ ላይ እንዳለ አረፋ ጠፍታለች።
- 8
የእስራኤል ኃጢአት የሆኑት የአዌን የኮረብታው መስገጃዎች ይፈርሳሉ፤ እሾህና አሜከላ በመሠዊያዎቻቸው ላይ ይበቅላል፤ ተራሮችንም። ክደኑን፥ ኮረብቶችንም። ውደቁብን ይሉአቸዋል።
- 9
እስራኤል ሆይ፥ ከጊብዓ ዘመን ጀምረህ ኃጢአትን ሠርተሃል፤ በዚያ ጸንተዋል፤ በጊብዓ ላይ ሰልፍ አይደርስባቸውምን?
- 10
በፈቀድሁም ጊዜ እገሥጻቸዋለሁ፤ ስለ ሁለቱም ኃጢአታቸው በታሰሩ ጊዜ አሕዛብ ይሰበሰቡባቸዋል።
- 11
ኤፍሬም ማበራየት እንደ ለመደች ጊደር ነው፥ እኔ ግን በአንገቱ ውበት እጫንበታለሁ፤ በኤፍሬም ላይ እጠምድበታለሁ፥ ይሁዳም ያርሳል፥ ያዕቆብም አፈሩን ያለሰልሳል።
- 12
እግዚአብሔር መጥቶ ጽድቅን እስኪያዘንብላችሁ ድረስ እርሱን የምትሹበት ዘመን ነውና ለእናንተ በጽድቅ ዝሩ፥ እንደ ምሕረቱም መጠን እጨዱ፥ ጥጋታችሁንም እረሱ።
- 13
ክፋትን አርሳችኋል፥ ኃጢአትንም አጭዳችኋል፥ የሐሰትንም ፍሬ በልታችኋል፤ በኃያላንህ ብዛት፥ በመንገድህም ላይ ታምነሃልና።
- 14
በሕዝብህም መካከል ሽብር ይነሣል፤ እናትም ከልጆችዋ ጋር በተፈጠፈጠች ጊዜ ሰልማን ቤትአርብኤልን በሰልፍ ቀን እንዳፈረሰ፥ አምባዎችህ ሁሉ ይፈርሳሉ።
- 15
ከኃጢአታችሁም ክፋት የተነሣ ቤቴል እንዲሁ ያደርግባችኋል፤ በነጋ ጊዜ የእስራኤል ንጉሥ ፈጽሞ ይጠፋል።